በጅቡቲ በኩል የሚገቡ ሰዎች ኢትዮጵያ ውስጥ ለኮሮና መስፋፋት ስጋት ናቸው ተባለ

በጅቡቲ በኩል የሚገቡ ሰዎች ኢትዮጵያ ውስጥ ለኮሮና መስፋፋት ስጋት ናቸው ተባለ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በኮረና ቫይረስ በከፍተኛ ሁኔታ ከተጠቃችው ጂቡቲ የሚመጡ ኢትይጵያውያን ቁጥር መጨመሩን ተከትሎ፤ የበሽታውን ስርጭት ለመቆጣጠር የአፋርና አማራ ክልሎች ጥረት እያደረግን ነው ብለዋል።

“ከጅቡቲ ከበሽታው የሚሸሹ፣ እንዲሁም ጾም ስለሆነ ሙቀቱን ለማሳለፍ ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ በርካታ ሰዎች አሉ” ያሉት የአፋር ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ሓላፊ ያሲን ሙስጠፋ፤ መንግሥት የኮሮናቫይረስ መስፋፋትን ለመቆጣጠር በድንበሮች በኩል የሰዎች እንቅስቃሴን ቢያግድም ከጂቡቲ የሚገቡት ሰዎች ቁጥር ከዕለት ወደ ዕለት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መሆኑን አጋልጠዋል።

ከጅቡቲ በአፋር ክልል በኩል ወደ ኢትዮጵያ የሚያስገቡ አስራ አምስት የመግቢያ በሮች መኖራቸውንና ሦስቱ ዋና የሚባሉ እንደሆነ  የተናገሩት አመራሩ ከዚህ የተነሳ በሁሉም ላይ ስፍራዎች ላይ ቁጥጥር እየተደረገ እንደሚገኝ ከመግለጻቸው ባሻገር ፣ ከአፋር ክልል ጋር ወደሚዋሰነው የአማራ ክልል፣ የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞንም ተመሳሳይ በሆነ መልኩ ከጅቡቲ በኩል የሚገቡ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ይፋ አድርገዋል::

ሰዎቹ በእግር ድንበር ተሻግረው የሚገቡባቸው የተለያዩ ቦታዎች መኖራቸውን  ያመላከቱት የዞኑ የጤና ቢሮ ሓላፊ ካሊድ ሙስጠፋ ” በአማራ ክልል ለዚህ ችግር ከተጋለጡ ስፍራዎች አንዱ ባቲ ወረዳ ነው። ባቲ ላይ አቢላል የሚባል ስፍራ በእግርና በመኪና ሰዎች ስለሚገቡ የሙቀት ልኬት ጀምረናል” በማለት የቫይረሱን ስርጭት ለመቆጣጠር የሚያደርጉትን ጥረት አብራርተዋል።

በዞኑ ካሉት ሠባት ወረዳዎች ፣ አምስቱ ከአፋር ክልል ጋር ስለሚዋሰኑ ከጅቡቲ በአፋር በኩል የሚገቡ ሰዎች ቁጥር በርካታ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ፤ አራቱ ወረዳዎች ከኮሮናቫይረስ ጋር በተያያዘ የስጋት ቀጠና ናቸው በሚል ተለይተዋል::

በአፋር ክልል 18 የለይቶ ማቆያ ስፍራዎች መዘጋጀታቸውን  የገለፁት የክልሉ ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ያሲን ሃቢብ በበኩላቸው ፤ በሦስቱ ዋና ዋና መግቢያዎች በኩል ብዛት ያላቸው ሰዎች በመኪናና በእግር ስለሚገቡ ቫይረሱ እኔዳይስፋፋ ትኩረት መደረጉን ገልጸዋል። የአፋር ክልል መንግሥት ከጅቡቲ የሚመጡ ሰዎችን ለመቆጣጠር እያከናወነ ባለው ሥራ ፣ 380 የሚሆኑ ሰዎች ወደ ለይቶ ማቆያ ውስጥ እንዲገቡ መደረጉንም አስታውቀዋል::

LEAVE A REPLY