ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የቢጫ ወባ በሽታ መባባስን ተከትሎ ኢትዮጵያ ውስጥ 86 ሰዎች በበሽታው መያዛቸውን የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ገለፁ።
በሚኒስቴሯ መግለጫ መሠረት በደቡብ ክልል ጉራጌ ዞን እነሞር እና ኤነር ወረዳ ከየካቲት ወር መጨረሻ ጀምሮ የበሽታው ምልክት ታይቷል። ይህን ተከትሎ የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት ከክልሉ ጤና ቢሮ እና ከዞኑ ጤና መምሪያ ጋር በመተባበር የጤና ሚኒስቴር ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል።
የካቲት 24 ቀን 2012 ዓ.ም በሽታው መጀመሩን ያስታወሱት ዶክተር ሊያ ለመጨረሻ ጊዜ በበሽታው የተያዘ ሰው ሪፖርት የተደረገው መጋቢት 20 ቀን እንደነበር ከመጠቆማቸው ባሻገር እስካሁን 86 ሰዎች በበሽታው መያዛቸው እና አራት ሰዎችም ሕይወታቸው ማለፉን ዛሬ በፌስ ቡክ ገጻቸው ላይ አስነብበዋል።
በወረዳው በሽታው በስፋት በታየባቸው አምስት ቀበሌዎች የቤት ለቤት ቅኝት የተካሄደ ሲሆን፤ በዚህም 1 ሺህ 225 ቤቶች እና ሁለት ትምህርት ቤቶች በቅኝቱ መታየታቸው የተገለጸ ሲሆን፤ ለበሽታው ተጋላጭ ናቸው የተባሉ 27 ሺህ 178 ሰዎች የቢጫ ወባ ክትባት መከተባቸው ታውቋል።