ጃዋር መሐመድ የፖለቲካ ውሳኔ ይሰጥ ሲል፤ አብን ሕገ መንግስት ይሻሻል ብሏል
ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የኢትዮጵያ መንግሥት በዚህ ወቅት ዋነኛ ተገዳዳሪ ኃይል የሆነውን ኮሮና ቫይረስን ታሳቢ ባደረገ መልኩ፤ ምርጫን አስመልክቶ ያቀረባቸው አራቱም አማራጮች “የሕግ መሠረት የላቸውም” በማለት ጃዋር መሀመድ ተቃውሞውን አሰምቷል።
የወረርሽኙን መስፋፋት ተከትሎ ቀጣዩን ምርጫ ለማካሄድ አስቸጋሪ በመሆኑ መንግሥት በበኩሉ መፍትኄ ናቸው ያላቸውን አራት አማራጮችን ለተቃዋሚ ፓርቲዎች ዛሬ አቅርቧል።
“ኮቪድ19፣ ምርጫን ማራዘም እና የሕግ አማራጮች” በሚል ርዕስ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት መንግሥት ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ውይይት አካሂዷል።
ሀገሪቱ በህገ መንግሥቱ መሠረት እስከ መጪው ነሃሴ ወር ማለቂያ ድረስ አጠቃላይ ምርጫ የማካሄድ ግዴታ ቢኖርባትም ፣ የኮቪድ19 ወረርሽኝ ምርጫን ማከናወን ከማያስችል ደረጃ ላይ በመድረሱ ምክንያት ሕግና እውነታውን አጣጥሞ መሄድ አስፈላጊ ነው ተብሏል በውይይቱ።
የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ምክትል ዐቃቤ ሕግ ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ፤ ችግሩን ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በማያፋልስ መልኩ ለመቅረፍ፣ አራት የመፍትኄ አማራጮች መቀመጣቸውን ጠቁመው እነርሱም:-
1. የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን መበተን
2. የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ
3. ሕገ መንግሥት ማሻሻል
4. የሕገ መንግሥት ትርጓሜ መጠየቅ መሆናቸውን ለተሳታፊዎች አብራርተዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ አወዛጋቢው ፖለቲከኛ ጃዋር መሐመድ በመንግሥት በኩል የቀረቡት አራቱም አማራጮች አያዋጡም ሲል የመፍትኄ ሐሳቦቹን ውድቅ አድርጓል።
የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) አባል የሆነው (ምንም እንኳ ኦፌኮን የተቀላቀለበት መንገድ አግባብ ባይሆንም) ጃዋር መሀመድ፤ ምርጫውን በኮሮና ቫይረስ ምክንያት በታለመለት ጊዜ ማካሄድ አይቻልም በሚል የቀረቡት አራቱም አማራጮች አያዋጡም በማለት በይፋዊ የፌስቡክ ገፁ ላይ ሐሳቡን በግልፅ አስቀምጧል።
ጃዋር መሀመድ “አራቱም አማራጮች ሕጋዊ መሠረት የላቸውም፤ መፍትኄው ሕጋዊ ሳይሆን ፖሊቲካዊ ስምምነት መፍጠር ነው” ሲልም አስተያየቱን አስፍሯል።
ይህንን ተከትሎ በጽንፈኛነት የሚከሰሰው ጃዋር አሁንም ብጥብጥና ሁከት ለመቀስቀስ እየተንደረደረ ነው የሚሉ አስተያየት ሰጪዎች ወቅቱን ያላገናዘበና ወረርሽኙን የመቋቋም ፈተና የተደቀነበት መንግስት ግርግር እንዲያነሳ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርግ መክረዋል።
በሌላ በኩል አብን (የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ) በበኩሉ ሕገ መንግስቱን የማሻሻል ጊዜዉ አሁን ነው በሚል ባወጣው መግለጫ አንቀጽ 39ኝ ጨምሮ የተለያዩ 15 እንቀጾቸን በመጥቀስ እንዲቀይሩ ጠይቋል