በጎጃም ትናንት ምሽት በተካሄደ ሠርግ ላይ በፈነዳ ቦምብ ሁለት ሰዎች ሞተው አራት...

በጎጃም ትናንት ምሽት በተካሄደ ሠርግ ላይ በፈነዳ ቦምብ ሁለት ሰዎች ሞተው አራት ቆሰሉ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በአማራ ክልል በምስራቅ ጎጃም ዞን፣ እናርጅ እናውጋ ወረዳ “ሲማ ቀበሌ” የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በተላለፈ መልኩ ትናንትና በተካሄደ የሠርግ ሥነ ሥርዓት ላይ በፈነዳ ቦንብ ሁለት ሰዎች መሞታቸው ተሰማ።

ትናንት ምሽት በተከናወነው ሠርግ ሕይወታቸውን ካጡትበተጨማሪ አራት ሰዎች ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው መሆኑን የእናርጅ እናውጋ ወረዳ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሓላፊ ወይዘሮ ጥሩ ሴት መንግሥት አረጋግጠዋል።

ከሟቾቹ አንዱ የሆኑት እና ቦንቡን ይዘውት የነበሩት ግለሰብ የሠርገኞቹ ቤተሰብ ሲሆኑ በአጋጣሚ የደረሰ ጉዳት እንጂ ሆን ተብሎ አለመሆኑን የጠቆሙት ሓላፊዋ ፤ ጉዳት ደረሰባቸው ግሰቦች የሕክምና እርዳታ እየተደረገላቸው መሆኑን ገልጸዋል። መንግሥት የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመቀነስ ከአራት በላይ ሰዎች የሚሰበሰቡባቸው እንደ ሠርግ ያሉ ዝግጅቶች እንዳይካሄዱ መከልከሉንና በወረዳው ሠርግ እንዳይደገስ ርብርብ እየተደረገ መሆኑንም አስረድተዋል።

“ግለሰቦቹ ሠርግ እንደማይፈቀድ ተነግሯቸው ፣ አሾልከን ዳርን በሚሉበት ወቅት ነው እንግዲህ ጉዳት የደረሰው። ሠርጉ ላይ ብዙ ሰው አልነበረም። ቦንብ የያዘውና  ሕይወቱ የጠፋው ግለሰብም አማች ነው ፣ ሠርጉ እንዲቆም ትዕዛዝ ከተሰጠ በኋላ ነው ፣ ይህንን ድርጊት ሲፈጽም ጉዳት የደረሰው” በማለትም በኅብረተሰቡ ዘንድ የግንዛቤ እጥረት መኖሩን  የኮሚኒኬሽን ባለሙያዋ አመላክተዋል።

LEAVE A REPLY