ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን በመተላለፍ የተገኙና ክስ የተመሠረተባቸው ዘጠኝ ግለሰቦች መቀጣታቸውን ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አስታውቋል፡
ተከሳሾቹ ሚያዝያ 9 ቀን 2012 ዓ.ም፣ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 13 ውስጥ በሚገኝ አንድ ጠባብ ክፍል ቤት ውስጥ፣ ዘጠኝ ሆነው ተሰብስበው ጫት ሲቅሙ የተያዙ እንደሆኑ ተገልጿል፡፡
በዚህም ምክንያት ጫት በማስቃምና ከአራት ሰው በላይ በመሆን በመሰብሰባቸው ፣ ግለሰቦቹ ተከስሰው ፍርድ ቤት ቀርበው እንደነበር ተሰምቷል፡፡
ፍርድ ቤቱም ጉዳዩን በተፋጠነ ችሎት መዝገቡን መርምሮ፣ ተከሳሾቹም የወንጀል ድርጊቱን መፈፀማቸውን በዝርዝር በማመናቸው፤ ሚያዚያ 19 ቀን 2012 ዓ.ም በዋለው ችሎት እያንዳንዱ ተከሳሽ ሦስት ሺኅ ብር መቀጮ እንዲቀጡ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ 78 ሰዎች የኮቪድ 19 ቫይረስን ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ በመተላለፍ በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተጣራባቸው እንደሚገኝ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ይፋ አድርጓል፡፡