ሚያዝያ 2012
እስክንድር ነጋ እንደገና ታሰረ! በአለፉት አርባ ዓመታት ውስጥ እንዳወቅሁት፤ እሰክንድር ሌባ አይደለም፤ እስክንድር ወንጀለኛ አይደለም፤
እስክንድር የራሱ የሆነ ችግር ያለበት ይመስለኛል፤ ስንት የተመሰከረለት ሌባ ደረቱን ነፍቶ በኩራት በሚሄድበት አገር ለምን በአገርህ ጉዳይ ሀሳብህን ገለጽህ ተብሎ ሲታሰር በሥልጣን ወንበሩ ላይ የሚለዋወጡት ሁሉ አንድ የሚጋሩትና የማይለቅ በሽታ እንዳለባቸው ያመለክታል፤ አገሪቱ ከእኛ ሌላ ባለቤት የላትም የሚል አጉል እምነት አላቸው፤
እስክንድር ስሕተት የለበትም ማለት አልችልም፤ ነገር ግን ዓቢይ የይሁዳ አንበሳን በወፍ ሲለውጠው ያልታሰረ የማይመች ነገር ተናግረሃል ብሎ እስክንድርን ማሰር ለእኔ ክፉ መልእክት አለው፤
የሰው ልጅ በሚናገረውና በሚያደርገው እግዚአብሔር ቢቆጣ ጉልበት አለኝ ብሎ የሰውን ልጅ ድምጥማጡን ያጠፋው ነበር፤ ለኔ ትልቁ ጥያቄ ወንጀለኞችን የሚፈራ አገዛዝ ሰላማዊ ሰውን የሚፈራው ለምንድን ነው?