ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በአፍሪካ ግዙፉ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ አራት ቦይንግ 777 – 300ER የመንገደኞች አውሮፕላኖቹን ወደ ዕቃማጓጓዣነት እንደቀየራቸው ገለፀ፡፡
አየር መንገዱ ከ80 በላይ ዓለም ዐቀፍ የመንገደኞች በረራዎቹን በኮሮና ቫይረስ የተነሳ መሰረዙን ጠቁሞ የዕቃ ማጓጓዝ አገልግሎቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ግን ይፋ አድርጓል፡፡ ተቋሙ ይህን ለማድረግ እንዲያግዘው አራት ቦይንግ ስሪት የሆኑ የመንገደኞች አውሮፕላኖቹን ወደ ዕቃ ማጓጓዣነት ቀይሪያለሁ ብሏል፡፡
በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቻይናዊው ቢሊየነር ጃክ ማ ለአፍሪካ አገራት የተበረከቱ የኮሮና መከላከያ ቁሳቁሶችን እያጓጓዘ ነው። የዓለም ምግብ ፕሮግራም አዲስ አበባን ለአፍሪካ አህጉር የእርዳታ ማሰራጫ ማዕከል አድርጎ መምረጡም ለአየር መንገዱ የካርጎ አገልግሎት ተጨማሪ ገቢ ማግኛ መንገድ ይሆንለታል ነው የተባለው፡፡