ስያሜ የክርክሮች መሠረት መሆኑን ታላቁ ሶቅራጥስ አስረድቷል። አብዘኛዉን ግዜ ሰዎችን የሚያጨቃጭቀዉ አንድን ጉዳይ በተለያዩ ስያሜዎች መጥራት ነዉ። ሁሉም ለክርክሩ በሚያመች መንገድ ነገሮችን ወይም ሁኔታዎችን ይሰይማል። በዝህ ምክንያት ጉልበት፣ ጊዜና ገንዘብ ይባክናል። ጠቃሚ ክርክር ለማድረግ በጉዳዩ ስያሜ ላይ መስማማት ግድ ይላል። ያለበለዝያ ጭቅጭቅ ይሆናል።
በኢፌዴሪ ህገ-መንግስት መሠረት ኢትዮጵያ በዝህ ዓመት መጨረሻ ምርጫ ማካሄድ አለባት። ግን በኮሮና ምክንያት የምርጫ ጊዜን ማራዘም ግድ ሆኗል። ይህን ለማድረግ የሚያስችል ግልፅ ህገ-መንግስታዊ ድንጋጌ ደግሞ የለም። ይህ ሁኔታ በሌሎች ሀገሮችም አጋጥሞ ያዉቃል። ስያሜዉ ደግሞ ህገ-መንግስታዊ ክፍተት ይባላል። በዝህ ስያሜ የህግ ምሁራንም ይስማሙበታል። ግራዝማች ግሪሳ ደግሞ “ህገ-መንግስታዊ ቀዉስ” ብሎታል።
ለሁኔታዎች ወይም ለነገሮች የሚሰጠዉ ስያሜ ከጀርባ ያለዉን ፍላጎት ያመላክታል። ግራዝማች ግሪሳም ህገ-መንግስታዊ ክፍተትን “ህገ-መንግስታዊ ቀዉስ” ያደረገዉ ለዝህ ይመስላል። ያ ካልሆነ “የሽግግር መንግስት” ብሎ ከበሮ ለመምታት ይቸገራል። ህገ-መንግስታዊ ቀዉስ በፖለቲካ ችግር ምክንያት በህገ-መንግስቱ መሠረት ሀገርን መምራት ሲያዳግት ይፈጠራል። አሁን የገጠመን ችግር ግን በግልፅ ከፖለቲካ ይለያል። ግራዝማች ግን ለፍላጎቱ ሲል ኮሮናን ፖለቲካ ያደርጋል። በተለመደዉ ካልኩሌተር “ክፍተትን” ወደ “ቀዉስ” ቀይሯል። አባቶች “ሊበሏት ያሰቧትን ጭልፊት ጅግራ ይሏታል” ያሉት ይህን ሁኔታ በተጨባጭ ይገልፃል። የአባቶቻችን የቀደመ ስልጣኔ እና ግንዛቤ በጣም ይደንቃል!
ለማንኛዉም ህገ-መንግስታዊ ክፍተት እንጂ ህገ-መንግስታዊ ቀዉስ የለም። ህገ-መንግስታዊ ክፍተት ደግሞ በህገ-መንግስታዊ መፍትሔ ይሞላል። ቁልፉ ጉዳይ ህገ-መንግስታዊ አማራጮችን ማወዳደር ብቻ ይሆናል።
ሠላም ዋሉ!