ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ሱዳን የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ የኮሮና ቫይረስ ሥርጭትን ለመቆጣጠር፣ በሱዳን መንግሥት እየተወሰዱ በሚገኙ እርምጃዎች ምክንያት፣ በቀን ገቢ ቤተሰቦቻቸውን ለሚያስተዳድሩ ኢትዮጵያውያን ተገቢው እርዳታ እየተደረገላቸው ነው ተባለ።
በዚህ የእርዳታ ማሰባሰቢያ 10,350 የአሜሪካን ዶላር የተሰበሰበ ሲሆን፤ 26,000 የሱዳን ፖውንድ ገንዘብም ተሰብስቦ ለተረጂዎቹ በምርት ተቀይሮ ተሰጥቷቸዋል:: ዱቄት፣ ዘይት፣ መኮሮኒ፣ ሩዝ፣ ስኳር ችግር ላይ ናቸው ለተባሉት ኢትዮጵያውያን በነፍስ ወከፍ ድጋፍ መደረጉን በሱዳን የኢትዮጵያ ኤምባሲ አምባሳደር ሽፈራው ጃርሶ ተናግረዋል::
አምባሳደሩ በውጭ ጉዳይ ሚንስትር በኩል ይፋ ባደረጉት መልዕክት ፤ ለችግር ለተጋለጡ አስቸኳይ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው 800 ዜጎችን የመለየት ሥራ መከናወኑንም ገልፀዋል።
በተለያዩ ዓለም ዐቀፍ ድርጅቶች ውስጥ የሚሠሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን፣ የተለያዩ የኮሚዩኒቲ አደርጃጀቶች፣ በጎ አድራጊ ድርጅቶችን እና የሃይማኖት ተቋማትን በማስተባበር ለእርዳታ ድጋፉ ሥራ ተሠርቷል መባሉንም ከመግለጫው መረዳት ችለናል።
በበረሃ ለነበሩና ከሥራ ተፍናቅለው ካርቱም ለመጡ 38 ለሚሆኑ ዜጎች የቤት ኪራይ እና የምግብ ቁሳቁስ ድጋፍ የተደረገ ሲሆን፤ እርዳታውን ለሁሉም እንዲደርስ ለማድርግ አቅም ስለማይፍቅድ ለችግር የተጋለጡትን ለመርዳት በየአካባቢያቸው ባለው ኮሚዮኒቲ በኩል ለከፋ ችግር የተጋለጡትን በመለየት እርዳታው እንዲቀርብ መደረጉም ተገልጿል።