ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በአማራ ክልል የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ተከትሎ በመጣው የሕዝብ የመገበያየት ፍላጎት መጨመር ሳቢያ በሸቀጦች ላይ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ ማድረግን አሁንም መቆጣጠር አልተቻለም ተባለ።
የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ እንዳለው ፤ የኮሮና ቫይረስን ምክንያት አድርገው በሸቀጦች ላይ ያልተገባ ዋጋ የሚጨምሩ ነጋዴዎች አሁንም አሉ። የቢሮው የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ አቢታ ገበያው ነጋዴዎቹ ዋጋ እየጨመሩ ያሉት ለቁጥጥር የተሠማሩ ባለሞያዎችን እግር እየጠበቁ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
የአማራ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ በዚህ መሠሉ ተግባር ተሠማርተው ከተገኙ ነጋዴዎች መካከል ከ7 200 የሚበልጡትን ሱቅ እንዳሸገ የጠቆሙት አቶ አቢታ፤ ተደጋጋሚ ምክርና ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸው ሊታረሙ ያልቻሉ 13 ነጋዴዎች ፍቃድ ደግሞ መሠረዙንና በ244ቱ ላይ ክስ መመሥረቱን አስረድተዋል።
ክስ ከተመሠረተባቸው ነጋዴዎች መካከል ፍርድ ቤት ቀርበው ከ3 ወር እስከ አንድ ዓመት የሚደርስ እስር የተወሰነባቸው መኖራቸውን፣ እነዚህ ሁሉ የቁጥጥር ሥራዎች እየተሠሩም በሸቀጦች ላይ የሚደረግ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ አሁንም በክልሉ እንዳልቆመ መረዳት ችለናል።