የትግራይ ሕዝብ ከማዕከል የሚደርስበት ተጽእኖ ተፈቷል ብሎ ሲያምን፣ ፊቱን ወደ ራሱ አመራር ማዞሩ አይቀርም። ” አቶ ሴኩቱሬ በትግራይ ሚዲያ ሃውስ ከሰጡት ቃለ መጠይቅ የተወሰደ።
የትግራይ ሕዝብ ጥያቄ ለአንዳንዶች መጠቀሚያ እንደሆነው መገንጠል ሳይሆን እንደ ማንኛዉም ኢትዮጵያዊ በእኩልነት ተከባብሮ መኖር እንደሆነ ግልጽ ነው። ከዚህ ቃለ መጠይቅ የምንረዳው ቁም ነገር ቢኖር ግን የትግራይ ሕዝብ የሕወሃት አንዳንድ አመራሮችን አቋም ከወዲሁ መታገል ካልጀመረ በስተቀር በቀጣይ ሌላ ዙር የሚያጠራው ትልቅ የቤት ስራ የሚጠብቀው መሆኑን ነው።
ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ወደ ብ/ጀ ተክለብርሃን ቃለ መጠይቅ ስንመለስ ጀነራሉ ከ27 ዓመት የቁጭት ዘመን በኋላ አቋማቸውን ለማስጨበጥ በአማርኛ እየተፍጨረጨሩ፣ አማርኛ መማሬ ይቆጨኛል ማለታቸው የጨቅላ ስነልቦናዊ ቀውስ (Infantile Political Disorder) ሆኖ አግኝቼዋለሁ። ትርጉም ከሌለው “የብሽሽቅ ፓለቲካ” ተነስተው ቁጭታቸውን በአማርኛ ከሚደሰኩሩ ይልቅ በቋንቋቸው ቢያቀርቡት ኖሮ ለአቋማቸው ጽናት ስንል፤ ከቁም ነገር በጻፍናቸው ነበር። ያ ግን አልሆነም። ይልቁኑ እልህ አስጨራሽ የሆነባቸው ነገር፤ ዛሬም ከእልፍ ሕዝብ ጋር መግባባት የቻሉት በአማርኛ መሆኑ ነው። “አልሞትኩም ብዪ አልዋሽም” ይሉሃል እንግዲህ ይህው ነው።
ከቋንቋው ብሽሽቅ በላይ አሳሳቢው ነገር “የትግራይ ሕዝብ የታገለው ለኢትዮጵያ አልነበረም፣ ትግራይን ነጻ ለማውጣት ነበር፣ የሚለው ትርክታቸው ነው። ጀነራሉ ትግሉ የማን ነበር፣ ለምን ተካሄደ፣ ምን አሳካ ለሚለው ዘመናት የፈጀ አውዛግቢ ጥያቄ አወዛጋቢ ምልከታ አቅርበዋል።
በዚህ አቋማቸውም የሕወሃት አመራሮችን እውነቱን ደብቃችኋል በማለት ሲከሱ ተቃዋሚዎችን ግን ድሮም ስጋታችሁ “እውነት ነበር” ብለዋል። ተቃዋሚው በዚህ ጉዳይ ነጻ ወጥቷል። ሕወሃቶች ግን ሃሳባቸው ከጀነራሉ ጋር ይሁን ወይም እስከዛሬ ከተናገሩት ጋር አቋማቸውን ግልጽ ማድረግ አለባቸው።
ጀነራሉ ይመሩት የነበረው የኢንሳ ኃላፊነትና ጀነራልነታቸውን የተቀበሉት ከትግራይ ሳይሆን ከኢትዮጵያ መንግስት እጅ ነው። ትምህርታቸው፣ ልምዳቸው፣ ሹመታቸውን ጨምሮ በግል ያካበቱት ሃብት ሳይቀር ያፈሩት ነጻ ለማውጣት በተለይ ታገልኩለት ካሉት ትግራይ ሳይሆን ትግራይም አካል ከሆነችባት ከኢትዮጵያ ነበር። የዛሬን አያድርገውና፣
ሲጠቃለል ግን ቢያንስ፣ ቢያንስ የሕሊናዎ አደራ ቢቀር ለታገሉትና ለወደቁት ክብር ሲሉ መልስ መስጠት የሚገባዎት መሰረታዊ መፋለሶች አሉ።
1) 27 ዓመት ሙሉ ትግሉ የተካሄደው፣ ለብሔሮች እኩልነትና ኢትዮጵያን ከአምባገነኖች ለመታደግ እንደነበረ ሲደሰኮር ተኑሮ፣ ዛሬ ላይ በድንገት ትግራይን ለመገንጠል ብቻ እንደነበር እንዴት ሊገለጥልዎት ቻለ?
2) የትግሉ ሀገራዊ ፋይዳ፤ የትግራይ መገንጠል ብቻ እንደነበር የተገለጸልዎት “አልነቀልም ካሉት ስልጣንዎ በመነቀልዎትና እንደሚታማውም ” ሕወሃት ሀገር ሲመራ የነበረበት የፈላጭ ቆራጭነት” ዘመን ማብቃቱን ስለተረዱ ይሆን?
3) በተቃዋሚው ጎራ እንደሚቀነቀነውና እርስዎም እንዳነሱት ትግሉ ኢትዮጵያዊ ካልሆነ፣ ትግሉን ኢትዮጵያዊ ስታስመስሉት የነበረው፣ ኢትዮጵያን ከፋፍሎ በማዳከም የትግራይን ሕዝብ ከፍላጎቱ ውጭ፣ ከኢትዮጵያ የመነጠል ህልም ስለነበረዎት ነው? ይህንንስ ባለማሳካትዎ ድርጅትዎን ይወቅሳሉ?
4) ነጻ ያወጣናችሁ፣ መስዋእትነት የከፈልንላችሁ እኛ ሆነን እያለን ዛሬ ግን ተገፍተናል፣ በበቂ አልተካስንም ከሚሉት ጋር የእርሶ አቋም ተቃርኖንስ እንዴት ይመለከቱታል?
5) “ኢትዮጵያዊነትን” በዚህ ደረጃ እያጣጣሉ፣ ወሳኝ የሆነ ቦታ ላይ ተቀምጠው ማስተዳደርዎስ ምጸትና የሕዝብ ንቀት አይሆንም?
6) ትግሉስ ኢትዮጵያን በማካተቱ፣ ድርጅቴ አሳስቶኛል ብለው ያምናሉ?