ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባውን በዛሬው ዕለት አካሂዷል። በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የመሰብሰቢያ አዳራሽ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባው የተለያዩ ውሳኔዎችን መርምሮ ማፅደቁም ተሰምቷል።
ፓርላማው በዛሬ መደበኛ ስብሰባው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጠቅላላ ምርጫን በተመለከተ ያቀረበውን የውሳኔ ሐሳብን የተመለከተ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርትኳን ሚዴቅሳ የጠቅላላ ምርጫን በተመለከተ ለምክር ቤቱ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በቦርዱ የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ የመራጮች ምዝገባ የሚጀምረው ከሚያዚያ 14 ቀን 2012 ዓ.ም ቢሆንም፤ በሀገሪቱ ውስጥ በተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ሣቢያ በርካታ ሕዝብዊ እንቅሰቃሴዎች የተገደቡ በመሆኑ የምርጫው ጊዜው በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ማካሄድ እንደማይቻል የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ት ብርቱካን ተናግረዋል።
የምርክ ቤቱ አባላት በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ምርጫውን በተያዘለት ጊዜ ማካሄድ አለመቻሉን እንደሚገነዘቡና፣ የምርጫ ጊዜው እንዲራዘም ምክረ ሐሳብ ማቅረቡ ተገቢ ቢሆንም በሀገሪቱ የተከሰተው የኮሮና ቫይረስን ወረርሽኝ ነው ለማለት ይቻላል ወይ? የሚል አስገራሚ ጥያቄ ሲያቀርቡም ተስተውሏል።
በርካታ ቁጥር ያላቸው የምክር ቤት አባላት በሽታው ወረርሽኝ እንደሆነና መንግስት ወረርሽን መሆኑን አምኖ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከማወጁ በላይ ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ መዝጋቱንና ሕዝባዊ እንቅስቃሴዎችን መገደቡን ጠቁመው፤ ቦርዱ ያቀረበውን ውሳኔ ተቀብሎ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ መምራቱን አግባብ መሆኑን በመግለፅ የእርስ በርስ ክርክር አድርገዋል።
የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ፥ ቦርዱ ተጠሪነቱ ለምክር ቤቱ መሆኑንና የመጨረሻ ውሳኔም የምክር ቤቱ መሆኑን ጠቁመው የቀረበውን የመፍትሄ ሀሳብ ለድምጽ አቅርበዋል።
ይህን ተከትሎ ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የጠቅላላ ምርጫን በተመለከተ ያቀረበውን የውሳኔ ሐሳብ መርምሮ የመፍትኄ ሐሳብ እንዲያቀርብ ለሕግ፣ ፍትህና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቷል:: ምሪቱ በ3 ተቃውሞ፣ በ7 ድምፀ ተአቅቦና በአብላጫ ድምጽ የተላለፈ ውሳኔ ሆኗል።
ምክር ቤቱ በዛሬው ውሎው ከምርጫው ጉዳይ ቀጥሎ በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ እና በሳዑዲ የልማት ፈንድ መካከል ለሁለተኛው አገር ዐቀፍ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ ሳኒቴሽንና ሃይጂን ፕሮግራም ማስፈጸሚያ የተደረገውን የብድር ስምምነት በሙሉ ድምፅ አፅድቋል።
ኢትዮጵያ ከኮሪያ ኤክስፖርት – ኢምፖርት ባንክ ጋር ለአዳማ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የልህቀት ማዕከል መመስረቻ፤ ከሳዑዲ የልማት ፈንድ ለደብረ ማርቆስ – ሞጣ የመንገድ ሥራ ማሻሻያና ማሳደጊያ ፕሮጀክት፤ ከዓለም ዐቀፍ የግብርና ልማት ፈንድ ለቆላማ አካባቢዎች የኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ የተደረገውን የብድር ስምምነቶችንም እንዲሁ በሙሉ ድምፅ ማፅደቁ ተነግሯል።