ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ምርቶቻቸውን ለውጪ ገበያ ብቻ እንዲያቀርቡ ግዴታ ተጥሎባቸው የቆዮት በኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ያሉ አምራቾች በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ለሁለት ወራት ብቻ በአገር ውስጥ ገበያ እንዲሸጡ የተፈቀደላቸው መሆኑ ተሰማ።
የገንዘብ ሚኒስትር ዶክተር እዮብ ተካልኝ፤ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ለአነስተኛና መካከለኛ ተቋማት ብድር መስጠት የሚያስችለውን አስቸኳይ የብድር ማዕቀፍ ማዘጋጀቱን ጠቁመው ለአምራች ኅብረት ስራ ማኅበራት 1.5 ቢሊዮን ብር ብድር እንደሚሰጥም ገልፀዋል።
የኮሮና ቫይረስ የሚያስከትለውን የምጣኔ ሃብት ተጽዕኖ ለመቀነስ መንግስት የተለያዩ ውሳኔዎችን አመቻችቷል ያሉት ሚኒስትር፤ ከውሳኔዎቹ ውስጥም በተለይ ለአነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች በቂ የብድር አቅርቦት ማመቻት አንዱ ግንባር ቀደሙ መሆኑን አስታውቀዋል።
ተቋማቱ የወረርሽኙን ተጽዕኖ ተቋቁመው ምርትና ምርታማነታቸውን እንዲጨምሩና ለሚያጋጥማቸው ችግር መፍትኄ ለመስጠት እየተሞከረ ከመሆኑ ባሻገር፤ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ተቋማቱ በሚያቀርቡት ጥያቄ መሰረት በአጭር ጊዜ ውስጥ ብድር እንዲያገኙ የሚያስችላቸው አሠራር እንዲዘረጋ ማድረግ ደግሞ ተጨማሪ የመፍትኄ አካል ነው ተብሏል።
የኮሮና ወረርሽኝ ቀጥተኛ ተጎጂ ያደረጋቸው የንግድ ተቋማት በየወሩ ይከፍሉት የነበረው የተጨማሪ እሴትና የተርን ኦቨር ታክስን አጠራቅመው ሰኔ ላይ እንዲከፍሉ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ ያሳለፈ ሲሆን፤ ውሳኔው ተቋማቱ በእጃቸው በቂ ገንዘብ እንዲኖርና የተሻለ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ የሚያግዝ መሆኑንም ዶክተር እዮብ አስረድተዋል።