የ”እህተ ማርያም” ተከታዮች ማነጋገር እንዳልቻሉና ለደህነነቷም እንደሚሰጉ አስታወቁ

የ”እህተ ማርያም” ተከታዮች ማነጋገር እንዳልቻሉና ለደህነነቷም እንደሚሰጉ አስታወቁ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ባለፉት ወራት በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በአወዛጋቢነቷ የምትታወቀው፣ እህተ ማርያም በሚል ስም የምትጠራው፣ ወ/ሮ ትዕግስት ፍትህ አወቅ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ድንጋጌ በመተላለፍ በቁጥጥር ሥር  ብትውልም እስካሁን  ያለችበትን ሁኔታ ፈጽሞ ማወቅ እንዳልቻሉና ለማነጋገር እድሉ እንዳልገጠማቸው ገለፁ::

የአዲስ አበባ ፖሊስ በበኩሉ “እህተ ማርያም” ን መያዙን አምኖ  ጉዳዮዋ በምርመራ እየተጣራ መሆኑን  ይፋ አድርጓል፡፡

ከኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ጋር  ፈጽሞ ተቃራኒ በሆነ መልኩ አማኝችን የሚያሳስት ተግባር በመፈጸም በመላ ዓለም ካሉ ኢትይጵያውያን መሀል ተከታዮችን መመልመል የቻለችው ይህቺ ግለሰብ በህግ እንድትጠየቅ ሠፊ ቅስቀሳ ሲካሄድ መቆየቱ ይታወሳል::

ራሷን “ንግሥተ ነገሥት ዘ ኢትዮጲያ” ብላ የምትጠራውና “እህተ ማርያም ” በሚል ስም የምትታወቀው ወ/ሮ ትዕግስት ፍትህአወቅ፤ የኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ 19) ስርጭትን ለመከላከል፣ ለመቆጣጠር እና የሚስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ በወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የወጣውን መመሪያ በመጣስ በኮማንድ ፖስቱ ቁጥጥር ሥር ውላለች::

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለመነጋገር፣ ለመወያየት ወይም መሰል ተግባራትን ለማከናወን፤ የአንድ ቤተሰብ አባላት ከሆኑ ዉጪ አራት እና ከዚያ በላይ ሆኖ በአንድ ቦታ በአካል መገኘትን  ይከለክላል:: “ማርያም አዛኛለች” በማለት ወይዘሮ ትዕግስት ድንጋጌውን በመጣስ በአዲስ ከተማ ክ/ከተማ ወረዳ 4 “ሉባር ሆቴል ” ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሚገኝ መኖሪያ ቤቷ ውስጥ በርካታ ሰዎችን በሰበሰበችበት ወቅት ነው የተያዘችው፡፡

ወ/ሮ ትዕግስት ከዚህ ድርጊቷ ባሻገር “ኢትዮጵያ ውስጥ በሽታ የለም! ተቃቀፉ፣ ተሳሳሙ” የሚሉ  መልዕክቶችን በማህበራዊ ትስስር ገፅ በመልቀቅ፣ በርካታ የማህበራዊ ሚዲያ ተከታዮች የተሳሳተ ግንዛቤ ይዘው፤ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል ከሚወስዱት የጥንቃቄ እርምጃ እንዲዘናጉ የማድረግ ተግባር ፈጽማለች ሲል አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል።

“እህተ ማርያም” ወይም ወ/ሮ ትዕግስት ፍትህ አወቅ እንግሊዛዊት ስትሆን፣ የኢትዮጵያ ዜግነት እንደሌላት እና በ1986 ዓ/ም ከኢትዮጵያ ወጥታ በ2007 ዓ/ም (ከ21 ዓመታት) በኋላ ወደ ኢትዮጵያ እንደተመለሰች ተረጋግጧል:: በ2008 ዓ/ም የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ላይ የሚገኘውን አርማ በመቅደድና በማቃጠል፣ እንዲሁም በ2009 ዓ/ም ወደ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት በመሄድ “ታራሚዎችን ላስፈታ እመቤቴ ማርያም ልካኝ ነው የመጣሁት” በማለት ታራሚዎችን በማነሳሳት በፈፀመችው ህገ-ወጥ ድርጊት በቁጥጥር ስር ውላ እንደነበር  ይታወሳል፡፡

ሰምነኛ መወያያ የሆነችው ይህች ግለሰብ ከትናንት በስቲያ በኮማንድ ፖስቱ በቁጥጥር ሥር ብትውልም እስካሁን ድረስ ግን ያለችበትን ሁኔታ እንደማያውቁና ለደህንነቷም ስጋት እንደገባቸው ተከታዮቿ በአዲስ አበባ ለሚገኘው የኢትዮጵያ ነገ ዘጋቢ ተናግረዋል።

ዛሬ ማለዳ ወደ ከተማው ፖሊስ ኮሚሽን ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት የሄደው ሪፖርተራችን እንደገለፀው ከሆነ ከማለዳው ጀምሮ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ግቢ ዙሪያ “እህተ ማርያምን ልናይ ነው የመጣነው፣ እባካችሁ እናታችንን አንዴ እንያት” በማለት የሴትዮዋ ተከታዮች ለፖሊሶች ተደጋጋሚ ጥያቄ ሲያቀርቡ ታይተዋል።

በቁጥር ከ20 የሚበልጡ የወ/ሮ ትዕግስት ተከታዮች ግለሰቧ ከተያዘች ጊዜ አንስቶ በግልና በተናጠል ወደ ፖሊስ ኮሚሽኑ በመምጣት ያለመታከት የአገናኙን ጥያቄ ሲያሰለቹ መሰንበታቸውን የተናገሩ የፖሊስ ኮሚሽኑ አባላት  ሴትዮዋ ምርመራዋን ያልጨረሰች በመሆኑ ለጊዜው ከጠያቂዎች ጋር መገናኘት እንደማትችል ቢነገራቸውም ተከታዮቿ ፍቃደኛ ባለመሆን በአካባቢው ሲያንዣብቡ ውለው ምሽት ላይ እንደሚበታተኑ ለኢትዮጵያ ነገ ገልጸዋል።

LEAVE A REPLY