ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት (በተለይም በኮሮና ቫይረስ ዙሪያ ለመምከር) ዛሬ ጠዋት አዲስ አበባ መግባታቸው ታወቀ፡፡
ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፍወርቂ በቆይታቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጋር በሁለትዮሽ ግንኙነቶች ላይ እንደሚወያዩ የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረመስቀል በትዊተር ገፃቸው አስፍረዋል።
ማስታወቂያ ሚኒስትሩ ይህን ይበሉ እንጂ ኢሳይያስን በዚህ አስከፊ ወቅት እያንደረደረ ኢትዮጵያ ያመጣቸው ጉዳይ የኮሮና ቫይረስ መሆኑን ታማኝ ምንጮች ይናገራሉ:: ሁለቱ ሀገራት ከሃያ ዓመት በኋላ የከፈቱትን ድንበር ተከትሎ በሚደረጉ ጉዞዎች የተነሳ የኮሮና ቫይረስ ስርጭት በኢትዮጵያና ኤርትራ ውስጥ በተሽከርካሪነት ሊስፋፋ ይችላል የሚል ስጋት በከፍተኛ ሁኔታ መኖሩ ታውቋል::
ፕሬዚዳንት ኢሳይያስ ከዚህ በተጨማሪ ኢትዮጵያ ውስጥ በሚኖራቸው የሁለት ቀናት ቆይታ ስለ አንበጣ መንጋ እና ቀጠናዊ ጉዳዮች ዙሪያ ሠፊ ውይይት ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡