የጄ ቲቪ ሠራተኞች ደምዎዝ አልተከፈለንም አሉ ፣ የጣቢያው ባለቤት ጆሲ ተሰውሯል

የጄ ቲቪ ሠራተኞች ደምዎዝ አልተከፈለንም አሉ ፣ የጣቢያው ባለቤት ጆሲ ተሰውሯል

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በድምፃዊ ዮሴፍ ገብሬ (ጆሲ ኢን ዘ ሀውስ) ባለቤትነት የሚተዳደረው የ ጄ ቲ ቪ ኢትዮጵያ ሠራተኞች ያለ ደምዎዝ ክፍያ በከፍተኛ ሁኔታ እየተጉላሉ መሆኑ ታወቀ።

ሠራተኞች ሰሞኑን ከቴሌቪዥን ጣቢያው ባለቤት ድምፃዊ ዮሴፍ ገብሬ ጋር ተገቢውን ክፍያ ባለማግኘታቸው ውዝግብ ውስጥ ገብተው እንደነበርና የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ ሕጋዊ ግዴታውን ለመፈጸም ፍቃደኛ እንዳልሆነ አስታውቀዋል::

ይሁን እንጂ ዛሬ ከሀያ በላይ የሚሆኑ የ ጄ ቲ ቪ ኢትዮጵያ ሠራተኞች (ጋዜጠኞች፣ የካሜራና ኤዲቲንግ ባለሙያዎችና ሾፌሮች)  የነበረውን ቅራኔ ወደ ጎን በመተው፣ ልዮነቶችን በሠላማዊ መንገድ ለመፍታት እንደ ከዚህ ቀደሙ በሥራ ሰዐታቸው ወደ ሥራ ቦታቸው ቢሄዱም፣ ምንም ሳይነግራቸው ቢሮአቸው ተዘግቶ እንዳገኙት ተናግረዋል።

ሠራተኞቹ ምንም የሚያውቁት ነገር እንደሌለ፣ የጣቢያው ሥራ አስኪያጅ አርቲስት ዮሴፍ ገብሬን ለማናገር ቢሞክሩም ሊያገኙት አለመቻላቸውን፣ ድምፃዊው  በመኖሪያ ቤቱ ውስጥ እንደሌለና ለጊዜው ወዴት እንደተሰወረ ማወቅ አለመቻላቸውን ለኢትዮጵያ ነገ የአዲስ አበባ ዘጋቢ ገልፀዋል።

ጄ ቲ ቪ ኢትዮጵያ ከሳምንት በፊት በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት  ” ገቢዬ ስለቀነሰ፣  ለሠራተኞቹ መክፈል የምችለው የደምዎዛችሁን ግማሽ ብቻ ነው” በማለቱ ከሠራተኞቹ ጋር ውዝግብ ወስጥ መግባቱን ተከትሎ ባለፉት 5 ቀናት ስርጭቱ ሙሉ ለሙሉ ተቋርጧል።

በጣም ከፍተኛ የሆነ የስፖንሰር ገቢና የማስታወቂያ ክፍያ ከሚያገኙ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች መሀል አንዱ የሆነው ጄ ቲቪ ኮሮና ቫይረስ ከገባ ገና በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ጣቢያውን ለመዝጋትና ሠራተኞቹን ያለ ደምዎዝ ለመበተን መገደዱ በብዙዎች ዘንድ ግርምትን ፈጥሯል።

ውዝግቡን ተከትሎ የተከሰተውን አለመግባባት የቴሌቪዥን ጣቢያውን ባለቤት ዮሴፍ ገብሬን (ጆሲ) ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

LEAVE A REPLY