ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የጦር መሣሪያ ያለው ማንኛውም ተቋም ወይም ግለሰብ በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ውስጥ የማስመዝገብ ግዴታ እንዳለበት የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አሳሰበ ።
የጦር መሣሪያን የመያዝ፣ የመግዛትና የመሸጥ ሥርዓቱ በመንግሥት እውቅና ብቻ የሚያደርግ አዲስ አዋጅ ሥራ ላይ እንዲውል ተደርጓል:: አዋጁ በጦር መሣሪያ ዝውውርና አስተዳደር ላይ የነበረውን የሕግ ክፍተት እንደሚሞላ የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አዳነች ሀበቤ አረጋግጠዋል።
በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት በመንግሥት ሕጋዊነት የተሰጣቸው አካላት ዓዋጁን በማስተግበር የጦር መሣሪያ ያለው ግለሰብም ይሁን ተቋም ምዝገባውን የማድረግ ግዴታ እንዳለባቸው ጠቁመው፤ የጦር መሣሪያ የያዘ፣ ያስመዘገበ ሁሉ እንዲይዝ እንደማይፈቀድና ፈቃድ የሚሰጠው ተቋም ወይም ግለሰብ በአዋጁ መመሪያ ሕጋዊየሚያደርጉትን መስፈርት አሟልቶ መገኘት ይጠበቅበታል ብለዋል።
አዋጁ የአገር ውስጥ ድርጅቶችንና ሌሎች አካላትንም የሚያይበት ሕጋዊ አካሄድ አለው ያሉት ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጓ ፤ማንኛውም በአገር ውስጥ የሚንቀሳቀስ ድርጅት የጦር መሣሪያ እንቅስቃሴውም ይሁን ይዞታው ሕጋዊነቱ የተረጋገጠና በውል የሚታወቅበት አሠራር ይዘረጋለታል ሲሉ ገልጸዋል። በኢትዮጵያ እስካሁን ድረስ የጦር መሣሪያዎችን የመሸጥና የማዘዋወር ህጋዊ እውቅና የተሰጠው አካል ባለመኖሩ ግዥና ዝውውሩ የሚካሄደው ህግን ባልተከተለ መንገድ መሆኑ ይታወቃል።