ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ረባዳማ እና የወንዝ ዳርቻ በሆኑ የኦሮሚያ አካባቢዎች በቀጣዮቹ ቀናት ጎርፍ ሊከሠት ይችላል የሚል ስጋት መኖሩ ተገለፀ።
በተጠቀሱት አካባቢዎች የሚገኙ ነዋሪዎች ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ የክልሉ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ምክር ለግሷል።
የክልሉ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ገረመው ኦሊቃ ፤ የብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲን ትንበያ ተከትሎ በአካባቢዎቹ ጎርፍ ሊከሠት ይችላል የሚል ስጋት መኖሩን ጠቁመዋል።
ብሔራዊ የሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ በቀጣዮቹ ቀናት በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች ጠንከር ያለ ዝናብ ይኖራል ማለቱ አይዘነጋም። አንዳንድ አካባቢዎች መደበኛ መጠን ያለው ዝናብ ያገኛሉ ያለው ኤጀንሲው በሌሎቹ ደግሞ ከመደበኛ በላይ የሆነ ዝናብ እንደሚጥልም ጠቁሟል።
ትንበያውን ተከትሎ ረባዳማና የወንዝ ዳርቻ በሆኑ የኦሮሚያ አካባቢዎች የሚኖሩ ሠዎች ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ መልዕክት እየተላለፈ እንደሚገኝ የጠቆሙትአቶ ገረመው ፤ ሠሞኑን የጣለው ዝናብ በክልሉ የተወሰኑ አካባቢዎች ጎርፍ እንዳስከተለም ገልጸዋል።
የሀርረጌ፣ አርሲ እና ቦረና ጥቂት ቦታዎች ጎርፉ የተከሰተባቸው ናቸው ቢሆንም እስካሁን በጎርፉ የከፋ ጉዳት እንዳልደረሰ ታውቋል።
በአዋሽ ተፋሰስ ምክንያት በክልሉ አምስት ዞኖች የሚገኙ 27 ወረዳዎች የጎርፍ ስጋት አለባቸው መባሉን ተከትሎየሚከሰተው ጎርፍ የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ ከወዲሁ እየተሠራ መሆኑ ተገልጿል።