ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ባለፉት ሀያ አራት ሰዐታት ለ1 ሺኅ 382 ሰዎች የላቦራቶሪ ምርመራ ተደርጎ 17 ሰዎች የኮሮና ቫይረስ እንደተገኘባቸው የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ገለፁ።
ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ሁሉም ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ፣ አሁን ላይ በኢትዮጵያ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 162 መድረሱን ሚኒስትሯ በፌስ ቡክ ገፃቸው አስረድተዋል።
ቫይረሱ ከተገኘባቸው ውስጥ ሰባቱ ከጂቡቲ የተመለሱና በአፋር አስገዳጅ ለይቶ ማቆያ ውስጥ የነበሩ ሲሆኑ፣ ስድስቱ ደግሞ ከሶማሊያ የተመለሱና በሶማሌ ክልል አስገዳጅ ለይቶ ማቆያ ውስጥ የነበሩ ናቸው። አራቱ በአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ የሆኑና ሁሉም የሌላ ሃገር የጉዞ ታሪክ የሌላቸው ናቸው ተብሏል።
ዛሬ በተደረገው የላብራቶሪ ምርመራ የኮቪድ 19 ቫይረስ ተጠቂ መሆናቸው የተረጋገጠው ከአራቱ ሰዎች ውስጥ የ27 ዓመቱ ወጣት የሥራው ባህሪ ተጋላጭነት ያለው ሲሆን፤ የ28 ዓመቷ ወጣት እና የ53 አመቷ ሴት ደግሞ ቫይረሱ ከተገኘበት ሰው ጋር ግንኙነት እንዳላቸው ተገልጿል።
የአፋር ክልል ነዋሪ የሆነውና አዲስ አበባ ከተማ የተገኘው የ39 አመቱ ኢትዮጵያዊ በቫይረሱ ከተያዘ ሰው ጋር ያለው ንክኪ እየተጣራ ይገኛል።
በዚህ ወቅት በኢትዮጵያ በለይቶ ህክምና ውስጥ ያሉ 63 ሲሆኑ፥ 93 ሰዎች ደግሞ ከቫይረሱ ማገገማቸውን የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ይፋ አድርገዋል።