ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመቆጣጠር ሲባል የተቀመጠውን ራስን በቤት ለይቶ ማቅየትን ተከትሎ በሴቶች ላይ የሚደርሰው ጥቃት በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል ተባለ::
የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር ዛሬ እንደ ገለፀው ከሆነ በመንግሥት የተቀመጠውን በቤት የመቅየት አማራጭ መንገድ በመጠቀም ራሳቸውን በቤት ውስጥ ያኖሩ ሴቶች በቅርብ ሰዎቻቸው ጥቃት እየተፈጸመባቸው እንደሚገኙ ነው የተነገረው::
የማኅበሩ ከፍተኛ አመራር የሆኑት ወ/ሮ ስምረት አንዳርጌ እንደገለፁት ከሆነ በቤት ውስጥ ቆይታን ተከትሎ በባሎቻቸው ፣ ወንድሞቻቸው ፣ በቅርብ ዘመዶቻቸውና ጎረቤቶቻቸው ጥቃት እንደተፈጸመባቸው የሚገልፁ ሴቶች ጥቆማ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል::
ሴቶቹ ከወሲባዊ ጥቃት እስከ ከፌተኛ ድብደባ የሚደርሱ የተለያዮ የሰብኣዊ መብት ጥሰቶች እየተፈጸሙ መሆናቸውን የሚናገሩት የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር ሓላፊ እየደረሰ ያለውን ጥቆማ ተከትሎ ወንጀለኞችን ለሕግ ለማቅረብና የጥቃቱንም መጠን ለመቀነስ ከሚመለከተው መንግሥታዊ አካልና ከኮማንድ ፖስቱ ጋር በጣምራ ለመሥራት ጥረት እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል::
የኢትዮጵያ ሴቶች የሕግ ባለሙያዎች ማኅበር ከሳምንታት በፊት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን መውጣት ተከትሎ በቤት ውስጥ ቆይታ አማካይነት በሴቶች ላይ የሚደርሰው ጥቃት ሊጨምር ይችላል ሲል ቅድመ ግምቱን መሰንዘሩ አይዘነጋም::