ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ከሞያሌ ለይቶ ማቆያ ከወጣው የኮሮና ተጠቂ ጋር ንክኪ ያላቸው ሰዎች በከምባታና ሀላባ ከተሞች እየተለቀሙ ነው
ከጥቂት ቀናት በፊት ከሞያሌ አስገዳጅ ለይቶ ማቆያ ማዕከል ተለቆ ሀላባ ቁሊቶ ከተማ ከተያዘው ግለሰብ ጋር ንክኪ ያላቸውን ግለሰቦች የማፈላለግ ሥራ በከፍተኛ ሁኔታ እየተካሄደ መሆኑን የከምባታ ጠምባሮ ዞን አስተዳደር ገለፀ::
የኮቪድ 19 ቫይረስ ተጠቂ መሆኑ እየታወቀ ከሞያሌ ለይቶ ማቆያ ማዕከል የተለቀቀው ግለሰብ ወደ ሀላባ ቁሊቶ በሚመጣበት ወቅት ያደረገውን ንክኪ ተከትሎ የተለያዮ ሰዎች ተይዘው ወደ አስገዳጅ ለይቶ ማቆያ የማስገባት ተግባር እየተከናወነ ነው ተብሏል።
በዚህም መሠረት ዛሬ በኮሮና ቫይረስ መያዙ የተረጋገጠው ግለሰብ ፤ በቅርቡ ከሞያሌ አስገዳኝ ለይቶ ማቆያ ወጥቶ ሀላባ ቁሊቶ ከተማ ከተያዘው ግለሰብ ጋር ንክኪ ያለው መሆኑንም መግለጫው ያመላክታል።
ይህ ግለሰብ ንክኪ እንዳለው ተጠርጥሮ ወደ አንጋጫ ለይቶ ማቆያ ማዕከል እንዲገባ ከተደረገ በኋላ ናሙናው ወደ ደቡብ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ተልኮ በተደረገው ምርመራ በቫይረሱ መያዙ ተረጋግጧል። ግለሰቡ በአሁኑ ወቅት በመልካም ጤንነት ላይ የሚገኝ ሲሆን ፤ ከእርሱ ጋር ንክኪ ያላቸውን ግለሰቦችን በማፈላለግ ወደ አስገዳጅ ለይቶ ማቆያ ማዕከል የማስገባት ሥራ እየተሠራ መሆኑ ተነግሯል።