ቅድመ ታሪክ
ልደቱ አያሌው የህዝብ ልጅ ነበረ።
ልደቱ በማንዴላ የተመሠለ የነፃነት ታጋይ ነበረ።
ምዕራፍ አንድ
ልደቱ አያሌው ‘ማንዴላ’ በሚባልበት ሰሞን” የዚህ ሰውዬ ነገር አላማረኝም ” ብዬ ብዙ ያገር በጎ አሳቢዎች ጋ ተቃቅሬ ነበር።
ሚያዚያ 30 1997 ነበር ።
በዚያ ቀን በልደቱ ብሔራዊ አርበኝነት ላይ ጥርጣሬ የነበረው ሰው ነበር ቢባል ማንም የሚያምን አይመስለኝም። ከዚያ ቀን በፊት እኔም አልነበረኝም።
የዚያን ቀን፤ በዚያ በስሜት አቅል በሚያስት ስሜታዊ ዕለት አቅሌንና ስሜቴን አሸንፎ የአንድ ሰው ሁኔታ በጥርጣሬ መንፈሴን አወከው፤ ቀላሉን አካብጄ ይሆን? በሚልም እስበሴ አሟገተኝ። ሰውዬው የዚያን ጊዜው ‘ማንዴላ’ ፤ የምንግዜውም ልደቱ ነበር ።
በዕለቱ የቅንጅት አመራሮች ሽማግሌው ፕሮፌሰር መስፍንን ጨምሮ ከህዝቡ ጎርፍ ጋር ተቀላቅለው በእግራቸው ወደ አደባባይ እየተጓዙ ነበር። በዚያ ለጠጠር ቦታ ይኖራል ተብሎ በማይታሰብበት የህዝብ ጭንቅንቅ መሀል አንዲት ቶዮታ ፒክአፕ መኪና አንገቱ ላይ ሶስቱን የሠንደቅ ቀለማት የያዘች ስካርፍ ጣል ያረገ ሰው ከላይ ጭና ማዕበሉን ሰንጥቃ ወደ መሀል በዝግታ መጓዝ ያዘች ።
መኪናዋ እጆቹን ለእቅፍ በሚጋብዝ አይነት በሰፊው ዘርግቶ ከሚጓዘው ሰው በስተቀር ከላይ ሌላ ሰው አልጫነችም። መኪናዋ የሠው እፍግታ ወደ ሚጨምርበት እየተጠጋች በመጣች ቁጥር የታዳሚው በስሜት የታጀበ ጩኸት እያየለ ሄደ
” ልደቱ ማንዴላ..ልደቱ ማንዴላ..”
ስሜቴ በህዝቡ ስሜት ተቃኝቶ የቀጠለው እሱ መሆኑን እስካረጋገጥኩበት እና እሱ ከሌሎች አመራሮች ተለይቶ ይህን ማድረግ ለምን አስፈለገው?? የሚለውን ማብላላት እስከጀመርኩበት ቅፅበት ድረስ ነበር ።
ምክንያቱም ያ ቀን የሡ ብቻ የድል ቀን አልነበረም።
ያ ቀን የቅንጅት ብቻ የድል ቀንም አልነበረም። ያ ቀን የዲሞክራሲ የልደት ቀን ነበር። የመላ ህዝቡ የድል ቀን ነበር።
ያ ቀን ሌላው ቀርቶ እስከምርጫው ቀን ድረስ ነፃ ምርጫ ለማካሄድ ቁርጠኛ መስሎ የነበረው የገዢው ግንባር እንኳ የድል ቀን ነበር። እንዲያውም በሡ ቦታ መለስ ዜናዊ እንደዚያ ሆነው ቢታዩ በተሻለ ያሳምነኝ ነበር ። ጀግና ብዬ ላወድስዎትም እችል ነበር።
ልደቱ ግን ለምን? ማንዴላ ምን ነካው? በዚህ ድርጊት በቅንጅት ውስጥ ዋናውን ወንበር እየጎተተ ይሆን?
ህዝቡ እያወደሰው ሲግተለተል እኔ ከራሴ ጋ ሙግት
ይዣለሁ። አካብጄ ይሆን? ወይስ ክፉ መንፈስ ተጠናውቶኝ ይህን የህዝብ ልጅ ቀንቼበት ይሆን? ወይስ እንዳሠብኩት ማንዴላ ለቅንጅት ዋና ወንበር በስተወንበሩ ደግሞ ምርጫውን ሲያሸንፉ የጠቅላዩን ቦታ ለመቆናጠጥ ስብዕናውን እየካበ ይሆን? (በወቅቱ ቅንጅት እንደሚያሸንፍ የማይገምት ጥቂት ህዝብና ብዙ ኢህአዲግ ብቻ ስለነበር)
ምዕራፍ ሁለት
ከሰልፉ በኋላ ከወዳጅ ዘመድ ጋ በጉዳዩ ተነታረኩኝ ያሳመነኝም ያሳመንኩትም ሰው አልነበረም ።
ለኋለኛው ኅሳቤ ማረጋገጫ ከማግኜቴ በፊት ለወራት
ልደቱ በህዝብ ልጅነቱ ቀጠለ። ለኔ ግምት ማረጋገጫ የሚሆን ትዝብት ከነፃው ሚዲያ ብከታተልም ምንም አላገኘሁም። ለወትሮው በቅንጅት ላይ ህዝብን የሚገለብጥ የፕሮፓጋንዳ ጥሬ ዕቃ የሚያነፈንፉት የገዢው ግንባር አቃቢያነ ፕሮፓጋንዳ እነ ሴኮ ቱሬም ጉዳዩን አላራገቡትም።
ምዕራፍ ሶስት
በመጨረሻም ለምርጫ የተቀናጁት ድርጅቶች ተዋህደው አንድ ፓርቲ “ቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ” ን ሊመሠርቱ ወሰኑ። ልደቱ የሚመራው ኢዴፓም የውህደቱ አካል መሆኑ ላይ ምንም የጥርጣሬ ፍንጭ አላሳየም።
ፓርቲው ሲዋሀድ መሪዎቹን መምረጥ ነበረበትና ለምርጫ ተሠየሙ ። አሁንም ከበስተ ልደቱ በኩል የአካሄድም ሆነ የቅድመ ሁኔታ ጥያቄ አልነበረም። እኔ ያቺ በፒክአፕ ላይ የተተወነችውን ስብእናን የማነፅ /personality cult/ ድራማ ውጤት አይቼ ራሴንም ልደቱንም ለመገምገም ተቁነጠነጥኩ።
ምርጫው ተጠናቀቀ
ኃይሉ ሻወል ሊ/መንበር
ብርቱካን ሚዴቅሳ ተቀዳሚ ም/ሊቀመንበር
ልደቱ አያሌው…. ም/ሊቀመንበር
ሙሉነህ ኢዮኤል ፀሀፊ ሆነው ተመረጡ።
አራቱ አመራሮች ማንዴላን ጨምሮ እጅ ለእጅ ተያይዘው በመድረክ ላይ በፈገግታ ሰክረው የሚያሳይ ፎቶ መላው የነፃ ፕሬስን አጥለቀለቀው። ህዝበ ኢትዮጵያም ሀሴት አደረገ።
ምዕራፍ አራት
በቀጣይ ካሉት ቀናት ባንዱ መላው የተቃውሞ ኃይሉን ያስደነገጠ ዱብዕዳ ተሠማ።
“ኢዴፓ የቅንጅቱን ውህደት የሚያረጋግጠው ሰነድ ላይ ማህተሜን አላሳርፍም አለ ።”
ከዚያች ቀን በኋላ ልደቱን ከመለስ ጋር እንጂ ከነ ብርሃኑ ነጋ ጋር አላየሁትም። ከበረከት ስምዖን ጋር እንጂ ከነ መስፍን ወ/ማርያም ጋር አላየሁትም። ልደቱ ከዚያች የምርጫ ቀን በፊት የቅንጅት ሰዎችን ሲቃወም ሰምቸው አላውቅም። ከዚያች ቀን በኋላም እነሱን ሲደግፍ አልሰማሁትም።
በፒክአፗ የሚፈልጋትን ወንበር አሳየ፤ በኃላፊነቷ ምርጫ ያቺን ወንበር ተበላ። እኔም የሱን ጉዳይ ፋይሉን ዘግቼ ወደ መዝገብ ቤት ላክኩኝ። እሱም እንደወጣ ቀረ…….
ድህረ ታሪክ
ከሰሞኑ ልደቱ አያሌው “የብሔር ብሔረሰቦች ልጅ” ሆኖ ተመለሠ።