ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የአስም ሕመምተኞች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ከመጣው ከኮሮና ቫይረስ ራሳቸውን አብዝዉ መጠበቅ እንዳለባቸው የሕክምና ባለሙያዎች አስታወቁ::
በጤና ሚኒስቴር የበሽታ መከላከልና መቆጣጠር ዳይሬክተር የሆኑት ወ/ሮ ሕይወት ሠለሞን የዘንድሮ ዓለም ዐቀፍ የአስም ቀንን ምክንያት በማድረግ ባስተላለፉት መልዕክት ላይ፤ የኮሮና ቫይረስ የአስም ሕመምን ሊያባብስ ስለሚችል ሕሙማን በቫይረሱ እንዳይጠቁ አስፈላጊዉን የመከላከል እርሚጃዎች ሊተገበሩ ይገባል ሲሉ መክረዋል፡፡
በመሆኑም በጣም አስፈላጊ ካልሆነ በስተቀር የአስም ታማሚዎች ከቤታቸው መዉጣት እንደሌለባቸውም ወ/ሮ ሕይወት አስታውቀዋል፡፡ የእትዮጵያ ቶራሲክ ሶሳይቲ ዋና ጸሐፊ ዶ/ር ራሄል አርጋው ፤ የአስም ታማሚዎች የሕመሙን ስሜት ከሚያባብስባቸው ማንኛውም ነገር እራሳቸውን መጠበቅ እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡
ሕመምተኞቹ ጭንቀትና ውጥረትን በማስወገድ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባቸው የገለፁት ዶ/ር ራሄል ፤ ሕመሙ ከበረታባችው የሕክምና ባለሙያ ማማከር እንዳለባቸውም ተናግረዋል፡፡ የአስም ሕመም ቀን ዛሬ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ተከብሮ ውሏል።