ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የአፍሪካ ልማት ባንክ ለኢትዮጵያ ታዳሽ ኃይል ልማት 10 ሚሊዮን ዶላር ብድር ፈቅጃለሁ አለ፡፡
በረጅም ጊዜ የሚከፈለው ይህ ብድር የተፈቀደው፣ በ”ቱሉ ሞዮ” አካባቢ ለሚገነባው የእንፋሎት ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት እንዲውል መሆኑም ተገልጿል።
በተለያዮ ፕሮጀክቶች ሀገራዊ ዕድገትን ለማስመዝገብ ተግታ እየሠራች ያለችው ኢትዮጵያ የታዳሽ ኃይል ቴክኖሎጂው የመጀመሪያው የእንፋሎት ኃይል አምራች እንደሚሆንም ብድሩን የፈቀደው የአፍሪካ ልማት ባንክ አረጋግጧል።
ፕሮጀክቱ የ50 ሜጋ ዋት የእንፋሎት ኃይል ማመንጫ ዲዛይን፣ ግንባታ፣ የሙከራ ሂደት፣ የኃይል አቅርቦት ሥርጭትና ማስተላለፍ ተግባራት ይከናወኑበታል። 11 ኪሎ ሜትር የሚረዝም የማስተላለፊያ መሥመር እንደሚዘረጋለትም ተነግሯል።
በአፍሪካ ልማት ባንክ ዋና የኢንቨስትመንት ኦፊሰርና የታዳሽ ኃይል ስፔሻሊስት አንቶኒ ካሬምቦ ፕሮጀክቱ አረንጓዴ ልማትን ለማስፋፋትና ለ600 ሰዎች ሥራ እንደሚፈጠር ከወዲሁ ፍንጭ ሰጥተዋል ።