ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የኢትዮጵያ ሠራዊት ሶማሊያ ውስጥ የኬንያን የጭነት አውሮፕላን መትቶ መጣሉን በሶማሊያ የአፍሪካ ኅብረት ሠላም አስከባሪ ኃይል አሚሶም ይፋ አደረገ።
የኢትዮጵያ ሠራዊት አንድ ክፍል የሆነውና የአሚሶም ኃይል አባል ቡድን አይደለም የተባለው የኢትዮጵያ ጦር ሶማሊያ ውስጥ አውሮፕላኑን መትቶ የጣለው ከአጥፍቶ ጠፊ ተልዕኮ ጋር ተመሳስሎበት እንደሆነም ተገልጿል። አምስት ሰዎችን ጭኖ ሲበር የነበረ አውሮፕላን በሶማሊያ ደቡብ ምዕራብ ግዛት የተመታው ሰኞ ሚያዚያ 26/2012 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ ነው።
አውሮፕላኑ ባርዳሌ በምትባል ከተማ በሚገኝ አየር ማረፊያ አቅራቢያ ተመትቶ የሁሉም ተሳፋሪዎች ሕይወት አልፏል። አውሮፕላኑ ተመቶ የወደቀበት ቦታን ተቆጣጥሮ የሚገኘው የአሚሶም ሴክተር ሦስት ኃይል አዛዥ የሆኑት ኮማንደር አለሙ አየነ ፤ በአካባቢው ያለው ጦር ሠራዊት ስለ በረራው የሚያውቁት ነገር እንደሌለ እና አውሮፕላኑነ ለማረፍ የሄደበት አቅጣጫ አጠራጣሪ እንደነበር ገልጸዋል።
በአካባቢው በሚገኘው አየር ማረፊያ አንድ አውሮፕላን ለማረፍ የሚሄድበት አቅጣጫ ከምሥራቅ ወደ ምዕራብ ሲሆን፤ ይህ በኢትዮጵያ ጦር ተመትቶ የወደቀው አውሮፕላን ግን ለማረፍ ሲበር የነበረበት አቅጣጫ በተቃራኒ አቅጣጫ ከምዕራብ ወደ ምሥራቅ እንደነበር ያስታወሱት ጀነራሉ ፤ በባርዳሌ የጦር ካምፕ ጥበቃ ላይ ያለው ጦራቸው አውሮፕላኑን መትቶ የጣለብትን ሦስት አስገዳጅ ምክንያቶችም አስቀምጠዋል።
አውሮፕላኑ ወደ ባርዳሌ ከተማ እንደሚበር መረጃ አለመብረሩ፣ አውሮፕላኑ ከተለመደው ውጪ ወደ ምድር ቀርቦ እየበረረ መሆኑ ፣ በካምፑ የሚገኘው ጦር አውሮፕላኑ ከተለመደው ውጪ ዝቅ ብሎ የሚበረው የአጥፍቶ መጥፋት ዒላማ እየፈለገ እንደሆነ መረዳታቸው የኢትዮጵያ ጦር አውሮፕላኑን ለመምታት መቻላቸውን ጀነራሉ ተናግረዋል ።
እንደ አሚሶም መግለጫ ከሆነ አውሮፕላኑ ለማረፍ ያደረገው ጥረት ባለመሳካቱ ለሁለተኛ ጊዜ ለማረፍ ሙከራ ሲያደርግ ሊመታ ችሏል። የአፍሪካ ኅብረት የሶማሊያ ሠላም አስከባሪ (አሚሶም ) አውሮፕላኑ ምንም እንኳ አየር ላይ ሳለ በኢትዮጵያ ሠራዊት ቢመታም፤ ለማረፍ በሚያደርገው ጥረት በጣም ወደ ምድር ተጠግቶ ስለነበረ ጎማዎቹን መዘርጋት ባለመቻሉ ያለችግር የማረፍ እድል አልነበረውም ሲል አጋጣሚውን በዝርዝር አስቀምጧል::
የደረሰውን አደጋ አስመልክቶ ማብራሪያ የሰጡት የሶማሊያ ደቡብ ምዕራብ ምክትል የትራንስፖርት ሚኒስትሩ ሐሰን ሁሴን ከአምስቱ ሟቾቹ መካከል ሁለቱ ሶማሊያውያን ሲሆኑ ሦስቱ ደግሞ ኬንያውያን ናቸው መሆናቸውን ማረጋገጫ ሰጥተዋል። ንብረትነቱ የአፍሪካን ኤክስፕረስ ኤርዌይስ የሆነው አውሮፕላን አደጋ እንዳጋጠመው በተነገረበት ወቅት በርካቶች በማህበራዊ ሚዲያ ላይ በኢትዮጵያ ጦር ተመትቶ መውደቁን ሲገልፁ መሰንበታቸው አይዘነጋም።