ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ኢትዮጵያ በመጪው ክረምት የታላቁ ህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌትን ለመጀመር ከያዘችው ዕቅድ እንደማታፈገፍግ አስታወቀች፡፡
በዕቅዱ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የመሩት ውይይት ዛሬ ተካሂዷል፡፡ በውይይቱ የውሃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትሩ ዶ/ር ኢንጅነር ስለሺ በቀለ የግድቡን ዝርዝር የሥራ ሂደት የተመለከተ ሪፖርት ቀርቦ ምክክር እየተደረገበት መሆኑም ተሰምቷል፡፡
በሪፖርቱ የግድቡ የሲቪል ምህንድስና ሥራው 87 በመቶ፣ ጥቅል የግንባታ ሂደቱ ደግሞ 73 በመቶ መድረሱ በሪፖርቱ ተሰምቷል። በዚህ መሠረት በሐምሌ ወር የመጀመርያውን የውሃ ሙሌት ሥራ ለማስጀመር የሚቻልበት የግንባታ ደረጃ ላይ በመደረሱ ተግባራዊ እንደሚደረግ ዶ/ር አንጂነር ስለሺ አስረድተዋል፡፡
የውሃ ሙሌቱ እንዳይጀመር ግብፅ ለተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ቅሬታ ማስገባቷን በተመለከተም ኢትዮጵያ ተገቢውን የምላሽ ሰነድ አዘጋጅታለች ያሉት ኢንጂነሩ፤ የዋሽንግተኑ መድረክ ለውይይት ክፍት ካልሆነ በስተቀር ኢትዮጵያ ወደ መድረኩ እንደማትመለስም አረጋግጠዋል።
የመጀመርያው ሙሌት ማስጀመርን በተመለከተ ከዚህ ቀደም በግብፅም ሆነ በሱዳን በኩል ስምምነት የነበር ቢሆንም አሁን ግን የሙሌት አተገባበሩን የሚገልፀውን ቴክኒካል ሰነድ እንዲላክላቸውና እንዲመለከቱት ሲጠየቁ በሁለቱም በኩል ፈቃደኛ አለመሆናቸው በውይይቱ ላይ ተጠቁሟል::
አትዮጵያ አሁንም የሦስትዮሽ ድርድሩ ቀድሞ በተቀመጡ መርሆች ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትኄ ሊሰጥ በሚችል መልኩ እንዲቀጥል ቢደረግ ፍቃዷ መሆኗና፤ ቀድሞም የምታራምደውን የጋራ ተጠቃሚነት መርህን እንደምትቀጥልም ተገልጿል::