ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ባለፉት 24 ሰዓታት ለ1 ሺህ 764 ሰዎች የላቦራቶሪ ምርመራ ተደርጎ 11 ሰዎች የኮሮና ቫይረስ እንደተገኘባቸው የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ገለፁ።
ዛሬ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ሁሉም ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ፥ 10 ወንዶች እና አንድ ሴት መሆናቸውን እና እድሜያቸው ከ18 እስከ 38 ዓመት መሆኑም ተሰምቷል።
ከዐሥራ አንዶቹ ውስጥ አምስቱ ከአዲስ አበባ ሲሆኑ ፣ሁለቱ ከትግራይ ክልል ለይቶ ማቆያ፣ ሦስት ሰዎች ከአፋር ክልል ለይቶ ማቆያ፣ እንዲሁም አንድ ግለሰብ ከኦሮሚያ ክልል አዳማ ለይቶ ማቆያ የተገኙ መሆናቸውን ሚኒስትሯ አስታውቀዋል።
የኮቪድ 19 ቫይረስ ከተገኘባቸው ውስጥ አምስቱ የውጭ ሀገር የጉዞ ታሪክ ያላቸው ሲሆኑ ፤ ሥድስቱ ደግሞ በቫይረሱ ከተያዘ ሰው ጋር ግንኙነት ያላቸው ናቸው ተብሏል።
በኢትዮጵያ ከቫይረሱ ጋር በተያያዘ እስካሁን ለ36 ሺህ 624 ሰዎች ምርመራ ተደርጎል። አሁን ላይ 138 ሰዎች በሕክምና ላይ ሲሆኑ፤ ሥድስት ተጨማሪ ሰዎች ደግሞ ከቫይረሱ አገግመዋል መባሉን ሰምተናል።