በአዲስ አበባ ማስክ ያላደረጉ ሰዎች በጅምላ በፖሊስ ሲታፈሱ ዋሉ

በአዲስ አበባ ማስክ ያላደረጉ ሰዎች በጅምላ በፖሊስ ሲታፈሱ ዋሉ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡- ዛሬ በአዲስ አበባ ከተማ የተለያዮ ስፍራዎች የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ማስክ (ጭምብል) አላደረጋችሁም በሚል ነዋሪዎች በጅምላ በፖሊሶች ሲታፈሱ ውለዋል።

ፖሊሶች በየትኛዋም የመኪናው አውራ መንገዶች ላይ ማስክ ሳያደርግ የሚዘዋወርን ሰው በሙሉ እያስቆሙ ያለ ምንም ማስጠንቀቂያ በፒክ አፕና በትላልቅ አውቶቢሶች እየጫኑ ወደ ፖሊስ ጣቢያና የተለያዮ ማጎሪያዎች ሲወስዱ መዋላቸውን የኢትዮጵያ ነገ የአዲስ አበባ ዘጋቢያችን አድርሶናል።

እርምጃው ድንገተኛና በመንግሥት በኩልም ቀደም ተብሎ ለሕዝብ የተሰጠ ይፋዊ መግለጫ አለመኖሩን ተከትሎ ፖሊሶች ማክስ ያላደረጉ ሰዎችን እያስቆሙ ወደ ጣቢያ ለመውሰድ መንገድ ላይ ሲያከማቹ፤ “ለምን እንዲህ ታረጋላችሁ?  ቢያንስ መግለጫ ሊሰጥ ይገባ ነበር፤ እባካችሁ ልቀቁን?” ያሉ  ሰዎችም በአዲስ አበባ ፖሊስና ታከለ ኡማ ባዋቀሩት “ተወርዋሪ” በተባለው ልዮ የፀጥታ ኃይል ሲደበደቡ ታይተዋል።

መንግሥት የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመቆጣጠር ያወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከህግ አግባብ ውጪ እየተጠቀሙበት ያሉት የአዲስ አበባና ፈደራል ፖሊስ አባላት ሰሞኑን አምሽተው የሚታዮ ወጣቶችን፣ ተጠጋግተው የተጓዙ ሰዎችን ከመምከር ይልቅ በወፍራም አጠና፣ በጎማና የመሣሪያ ሰደፍ ያለ ርህራሄ መቀጥቀጥን መደበኛ ሥራቸው አድርጎታል።

የኮሮና ቫይረስ መስፋፋትን ተከትሎ በአዲስ አበባ ከተማ በታክሲዎች፣ በሕዝብ ትራንስፖርት፣ ሕዝብ በሚበዛባቸው ቦታዎች  ማስክ ማድረግ አስገዳጅ ሆኖ መውጣቱ የሚታወቅ ቢሆንም፤ ሁሉም ሰው፣ በግሉ መኪና የሚንቀሳቀሰውም ሆነ፣ ሕዝብ ባልበዛባቸው አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱ በሙሉ ማስክ ማድረግ አለባቸው የሚል መመሪያ እስካሁን ድረስ አልወጣም፡፡

ዛሬ የታየው ይህን መሰሉ የሕግ ጥሰት ነው።  ፖሊስ ሰዎችን በጅምላ ከማፈሱ ባሻገር በየአደባባዮች ላይ እስኪበዙለት ድረስ በማስቀመጥና በከረረ ጸሐይ በማስመታት ሰብዓዊ መብታቸውን ሲጋፋ በግልፅ ታይቷል።  ከመንገድ ላይ የተያዙተና ወደ ተለያዮ ፖሊስ ጣቢያዎች ከተያዙት ውስጥ በሆስፒታል ለሚገኙ ታማሚዎችና አስታማሚዎች፣ ለእስረኞች ምግብ የያዙ በርካታ ሰዎች መኖራቸውንም በተለያዮ ቦታዎች አፈሳውን ተዘዋውሮ የታዘበው ሪፖርተራችን ዘግቧል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የከተማዋን ነዋሪዎች የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ማስክ አላደረጋችሁም በሚል ወደ ቅጣት እርምጃ እየገባ ያለው በየትኛው የሕግ አግባብ መሆኑን አስመልክቶ ከተለያዮ ራዲዮና ቴሌቪዥን ጣቢያዎች የተጠየቁት የፖሊስ ኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ሓላፊ ኮማንደር ፋሲካ ፋንታ ፤ የከተማዋ ፖሊስ እርምጃ እየወሰደበት ስላለው ህግ ከመናገር ተቆጥበው ፣ በጉዳዩ ላይ መግለጫ የሚሰጠው ጠቅላይ ዐቃቢ ሕግ፣ የሰላም ሚኒስቴር ወይንም የጤና ሚኒስቴር ነው የሚል ከእውነታው የራቀ ምላሽ ሲሰጡ ተደምጠዋል፡

ጠቅላይ ዐቃቢ ሕግ በበኩሉ “እነርሱን፣ የፖሊስ ኮሚሽኑን ጠይቁ” ያለ ሲሆን፤ የሠላም ሚኒስቴርም  “ጉዳዩን አጣርተን መልስ እንሰጣለን “የሚል ድፍን ያለ፣ የመንግሥት ሕግ አስፈጻሚ አካላት እርስ በርስ የተቀናጀ ሥራ እንደማይሠሩ ያሳዮበትን ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

LEAVE A REPLY