ዓመታዊው የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ክርስቲያን የረክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ጉባዔ ተጀመረ

ዓመታዊው የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ክርስቲያን የረክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ጉባዔ ተጀመረ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የረክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዕተ ጉባኤ ዛሬ መከፈቱ ተሰምቷል። ጉባኤው ሲከፈት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘ ኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘ አክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ይህ ወቅት ለሀገራችንም፣ ለቤተ ክርስቲያናችንም ሆነ ለህዝባችን ከባድ የፈተና ወቅት ነው ሲሉ ተደምጠዋል።

በእንዲህ ዓይነቱ ወቅት እንደ ትናንቱ የመሰለ አካሄድና አስተሳሰብ ጭራሽ የሚያስኬድ አይሆንም ያሉት ፓትርያርኩ፤ እኛ ሊቃነ ጳጳሳት እዚህ ላይ የተሰበሰብነው ህዝቡን በሁለንተናዊ ሕይወቱ ከፈተና ለመጠበቅ መሆኑን በውል የምንገነዘበው ነው።  ሕዝብ  አሁን ላይ በብዙ መልኩ እየተፈተነ ነው፤ ሕዝቡ በሰላም እጦት የህሊና ጭንቀት ላይ ነው የሚገኘው፤ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ በቀጣዮቹ ዓመታት በእጅጉ ሊጎዳ እንደሚችል የበሽታው ተጽዕኖ ምልክት እያሳየ ነው፤ የተከሰተው በሽታ መቼ ሊወገድ እንደሚችል የሚታወቅ ነገር የለም” በማለት የጊዜውን አሳሳቢነት አመላክተዋል።

በዚህ ሁሉ ተጎጂው ህዝብ እንደመሆኑ መጠን ይህ እንዳይሆን በተቻለ አቅም በጸሎት፣ በትምህርት፣ በምክርም፣ በማስታረቅም ሠፊ የማግባባትና የሕዝብ አድን ሥራ መሥራት አለብን ያሉት አቡነ ማትያስ፤ “አሁን ያለው ጥያቄ ሀገር እና ህዝብን ከፈተና የመታደግ ጥያቄ ነው፤ ይህንን ፈተና መሻጋገር የምንችለው በአንድነት ሆነን ስንቆም ነው። አንድነትን ለማምጣት ደግሞ የማግባባት ሥራ ግድ ይላል” ሲሉ መክረዋል።

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ እስካሁን ድረስ ቤተ ክርስቲያን፣ ሌሎች አብያተ ሃይማኖት፣ መንግሥትና ሕዝብ እንዲሁም የተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን በጋራ ሆነው በሠሩት ሥራ ቢያንስ ወረርሽኙ የከፋ አደጋ እንዳያደርስ በመከላከላቸው ምስጋና አድርሰዋል።

LEAVE A REPLY