ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡- በሀገሪቱ የውጪ ምንዛሬ ክምችትን ለመጨመር፣ ለዕዳ ስረዛ እና አደረጃጀትን ለመቀየር የሚደረጉ ጥረቶች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው ተባለ::
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የብሔራዊ ማክሮ ኢኮኖሚ ኮሚቴ አባላት ስብሰባ በዛሬው እለት መካሄዱን አስመልክቶ በፌስቡክ ገፃቸው ባሰፈሩት መረጃ ላይ ነው እንዲህ ያሉት።
ኮቪድ19 በኢኮኖሚ ላይ ያሳደረውን ጫና እና ለቀጣዩ የበጀት ዓመት የሚደረገውን የበጀት ዝግጅት በተመለከተ ውይይት ማድረጋቸውን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከዚህ በተጨማሪ የዓመቱን ኢኮኖሚያዊ ክንውን መገምገማቸውንም ገልጸዋል።
“ወረርሽኙ በዓለም ዐቀፍ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ላይ መቀዛቀዝ ቢያስከትልም፣ የተጀመሩ ፕሮጀክቶች እንዲሁም የበርካታ ዘርፎች አምራችነት እንዳይቋረጥ በሙሉ ዐቅማችን እንሠራለን” ሲሉ በጉባዔው ላይ መልዕክት ያስተላለፉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ፤ “የውጪ ምንዛሬ ክምችትን ለመጨመር እንዲሁም ለዕዳ ስረዛ እና አደረጃጀትን ለመቀየር የሚደረጉ ጥረቶችንም አጠናክረን እንቀጥላለን” ብለዋል:;