ተወልጄ ያደኩበት መንደር እንደ አብዛሃው የአዲስ አበባ አካባቢዎች የደከመ ቢሆንም፤ ጎረቤቶቻችን ከባድ ሚዛን ናቸው፡፡ በላይ በኩል የምንሊክ ቤተ-መንግስት ቡና አጣጪያችን ነው፤ በታች ደግሞ ከኢዮ-በልዩ ቤተ-መንግስት እሳት እንጫጫራለን፡፡
መቼም በድፍን ኢትዮጵያ ከፊት-በር በቀር፣ በሁለት ቤተ-መንግስቶች የተከበበ ጌታ እንጂ፣ ‹ጌቶ ሰፈር› አላውቅም፡፡ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ሁነኛ መገለጫም ነው፡፡ በገዢ እና ተገዥ መሀል ያለው ልዩነት ‹የመደብ› ተብሎ በቀላሉ አይታለፍም፡፡ ገነት እና ሲኦል በለው፡፡
ከጀርባ ማነው የሚያጎራብተን? …ድምጽህን ቀንሰ ስማኝ፡- የግብጽ ጉዳይ የሚቦካበት፣ አሜሪካ የምትታማበት፣ ከቻይና ቢሊዮን ረብጣውን የምትበደርበት፣ እንግሊዝን ሸውደህ፣ ከፈረንሳይ የምትጀናጀንበት፤ ደቡብ ሱዳንን የምትበዘብዝበት፣ ጅቡቲን የምታጃጅለበት፣ ኬኒያን የምታቄልበት፣ ኤርትራን የምታላምድበት… ውጭ ጉዳዩ ሚኒስትር ነው፡፡ የአፍሪካ ሕብረትም ከአንድ ኪሎ ሜትር በላይ አይርቅም፡፡
ሌላስ? አልክ እንዴ? ‹ካርታ ሥራዎች ድርጅት›ን እጠቅስልሀለሁ፡፡ በየቢሮዎቹ ያሉት የጥናት ወረቀቶች እንደ ግቢው ድባብ የመቃብር ስፍራ ፀጥታ የተጫነው እንዳይመስልህ? ከመቀሌ እስከ ባሌ፣ ከጎንደር እስከ ሐረር፣ ከወለጋ እስከ ጅጅጋ፣ ከዛላ-አንበሳ እስከ አማሬሳ… ያለች ሚጢጢ ሸጥ፣ ፈርፈር፣ ቦይ ሳትቀር ተመዝግቦበታል፡፡ ገዳሪፍ ያለች ቋጢኝ፣ ጎዴ ጫፍ የምትገኝ ኮረብታ፣ ከድንበር እስከ ሸገር ያሉ ሰፈሮች… በዝርዝር የሚያውቅ ተቋም ነው፤ ካርታ ሥራዎች ድርጅት፡፡
ወይ ፊትበር ስንቱን ይዘዋለች?!
‹አራት ኪሎ፣ አራት ኪሎ ፊት-በር፣ አራዳ
ዳኛው ክሴን ሰማኝ ቶሎ ቶሎ…› ሙዚቃን እየሰማህ)
ከቤታችን ፊት ለፊት በአዲስ አበባ (ምናልባትም በመላ አገሪቱ ሊሆን ይችላል) የመጀመሪያው የ‹ቦኖ ውሃ› አለ፡፡ መንደራችን ‹ቦኖ ሠፈር› የሚል መጠሪያ ያገኘው ከዚህ ነው፡፡ ዙሪያው በግንብና በብረት ታጥሯል፡፡ ለእንስራ (ባልዲ) ማስቀመጫ ከአርማታ የተሰራ አራት ማዕዘን ግንብ አለ፡፡ መሀሉ ላይ የእንስራ ሃውልት ይታያል፡፡ ውሃው የሚንቆረቆርበት ቧንባ ደግሞ በጥርብ ድንጋይ የተገነባ ነው፤ በመግቢያው በኩል ‹በዳግማዊ ምንሊክ ስም እየለመናችሁ ጥማችሁን አስወግዱ› የሚል ድንጋይ ላይ የተቀረፀ ጽሑፍ አለ፡፡ ክብር ለአባ ዳኘው!!
‹ቦኖ ውሃ› ለመድረስ አያሌ ጢሻና መሽሎኪያ ገባር መንገዶች ቢኖሩም፤ ዋናዎቹ ሦስቱ ናቸው::
ከታላቁ ቤተ-መንግስት ቁልቁል የሚወርድ ‹ጠከራራ›ን ዘቅዘቅ እንዳለ፣ ጉበታ መሰል ነገር ያለው መወረጃ ላይ ብቅ ሲል ይታያል:: ከታች መከላከያ ሚኒስቴርን ወደኋላው ትቶ የሚመጣው ደግሞ፣ ‹እናት ዳቦ ቤት›ን አልፎ፣ እቴጌ መስክን ታክኮ፣ ግዙፉ ‹ፖሊስ ገራዥ› የሠፈረበትን አቀበት ጨርሶ፣ ኑረዲን ሻይ ቤትና ሹፌር ሥጋ ቤት› ፊት ለፊት ወደአለው አደባባይ (ሊስትሮዎችና ጉሊት ቸርቻሪዎች የሚኮለኮሉበት ነው) ሲደረስ ትመለከተዋለህ::
በውጪ ጉዳይ ሚንስቴር ወይም በደህንነቱ ዋና ቢሮ ጀርባ፣ ‹ሾለቄ ሠፈር›ን አቋርጦ ወደ ውስጥ የሚያልፍ፣ ተዳፋቱ ላይ ባለው፣ በ‹ታህሳስ ግርግር› በጥይት ተደብድበው እንደ ‹ጄምስ ቦንድ› በተረፉት አወዛጋቢው ብ/ጄ መኮንን ደነቀ (ባንዳም ነበሩ ይባላል) ግቢ በኩል፣ ‹የቀበሌ 25 ጽ/ቤት›ን ጨርሶ ወደ ግራ ሲታጠፍ፣ ‹መተባበር ሆቴል› ሳይደርስ በአይንህ ራዳር ትቀልበዋለህ፡፡
በአሮጌው ቄራ፣ በደቦቃ፣ በጨርቅ ተራ፣ በ‹ሰው አትመን መላጣ›ው በር አልፎ የሚመጣው ደግሞ የፊት-በር አደባባይ ሲደርስ በቃኚ ጦር መነጽር ይመነጠራል፡፡
በርግጥ እኒህን እንቅስቃሴዎች ለመመልከትህ ግማሽ አፈር፣ ግማሽ ድንጋይ በሞላውና የሠፈሩ አነስተኛ ሜዳ በሆነው ገዥ ቦታ ላይ መቆም ይጠይቃል:: ከ‹ቦኖ ውሃ› ዝቅ ስትልህ የ‹በርታ ጠጅ ቤት› ኹካታና ግርግር፣ አንዲት ብርሌ እንኳ ሳትቀምስ በሞቅታ ይቀበልሀል፡፡ መሃል ላይ ‹ታዬ ተሰማ ግቢ› አለ፤ በለውጡ ሰሞን ህይወታቸው እንዳለፈ በወሬ ሰምቻለሁ፡፡ በላብዙ ርስትና ቤቶች ባለቤት እንደነበሩ ይነገርላቸዋል፡፡ ወራሾቻቸው የሚኖሩት እንደኛው ነው፡፡ እዚህ ጋ ደርግ ትርፍ ቤትና መሬት የወረሰበትን አዋጅ በወሽመጥ አስገባልኝማ፡፡
የሠፈሩ ቆሌ በ‹ታዬ ተሰማ› ስም ነው የምትጠራው፤ በልጅነት አእምሮዬ ቆሌ-አምላክ፣ አምላክ ቆሌ አድርጌ ስለማስብ አሟሟታቸው እንደ ክርስቶስ ይመስለኝ ነበር፡፡ ለረዥም ጊዜ ‹የታዬ ተሰማ አድባር ያውቃል› የሚሉ አሮጊቶችም ጥቂት እንዳልነበሩ አስታውሳለሁ፡፡
የምታደንቃቸውም ሆነ የምትረግማቸው በሙሉ የፊት-በር ነዋሪ ናቸው፡፡ ምንሊክም ሆኑ ኢያሱ፣ ዘውዲቱም ሆነች ተፈሪ፣ መንጌም ሆነ መሌ፣ ኃይሌም ሆነ አብቹ… የትም ይወለዱ ምን አገባኝ፤ ሰፈራቸው ፊትበር ነበር፤ ነውም እያልኩህ ነው፡፡
የምክትሎቻቸው ቢሮም እዛው ፊት-በር ነው፡፡ ፊት-በር ሁሉ በደጇ፡፡
ጥላሁን ገሠሠ፣ ግርማ ነጋሽ፣ ታማኝ በየነ… ፊት-በር ኖረዋል፡፡ የቅርቡን ዝነኞች እኗኳ ለጊዜው እንለፋቸው፡፡
የታዬ ተሰማ ግቢ አገልግሎቱ ብዙ ነው፡፡ ለሃዘንም ለደስታም ድንኳን መጣያ ነው፡፡ ለአዛውንቶችም እንደ ‹ድድ ማስጫ› ሆኖ ያገለግላል፡፡ ሴቶች ሰብሰብ ብለው ስለምን እንደሆነ ባላውቅም ሲንሾከሾኩበት አስተውያለሁ፡፡ ኮረዳዎች ‹ልታይ ልታይ…› የሚሉበት ኩሩ የመንደራችን አደባባይ ነው ልትለው ትችላለህ ነው፡፡ እኔና ጓደኞቼ ‹ቢቲ ጎል› ተጫውተንበታል፡፡ በአባሮሽ አለክልከንበታል፡፡ ‹ጨረቃ ድንቡል ቦቃን ዘፍነንበታል፡፡ በብይ ጉድጓድ ቡሄ የሸቀልኩበትን ተበልቼበታለው፡፡ በአዲስ አመት ማለዳ፣ ‹ለማኝ አሩን ሳያራ› ‹ፎርም› አድዬ ያገኘውትንም ተመንትፌበታለሁ፡፡
ሃሃሃ… ስንት ታሪክ አለው መሰለህ፤ (‹እንዳያልፉት የለም፣ ያ ሁሉ ታለፈ›ን አስታውስልኝማ?!)
የሆነ ሆኖ የታዬ ተሰማ ስትራቴጂካል ሜዳ በአመት አንዴ ‹ደረስኩ ደረስኩ…› በሚሉ አፍላ ጎረምሶችና ወደ ጉርምስና ለመሸጋገር ድንበር ላይ ባሉ ማቲዎች ቁጥጥር ሥር ይውላል፡፡ የግንቦት ልደታ ቀን፤ ድል ያለ አድባር ይደገስበታል፡፡ በዚህ እለት ድንጋይ እየወረወሩ አላፊ-አግዳሚውን የሚተናኮል፣ ‹እንኮዬ ድማሜ መቼ ነው ቅዳሜ› እያሉ ታላላቆችን የሚያበሽቅ የለም፡፡ ከጠጅ ቤት በሚወጣ የጠራራ ፀሀይ ሰካራም ላይም ማላገጥም በዚህ ቀን ያስቀስፋል፡፡ የሰፈሬ የተቀደሰች ቀን፣ አይ ግንቦት ልደታ!
በረባ ባረባ የሚራገሙ አሮጊቶች ድምጽም አይሰማም፡፡ ‹አቧራ አቦነናችሁ›፣ ‹መንገዱን ያዛችሁ›፣ ‹አጥሬን ልታፈርሱ ነው›፣ ‹ተነሱ ከዚህ ጋ›… በሚል የሚነጫነጩ እናቶች አይታዩም፡፡ ይልቁንም ቡናው ተፈልቶ፣ ቄጠሜው ተጎዝጉዞ፣ ቂጣው፣ ቆሎው ሙዚቃው ደምቆ እስክንጠራቸው በጉጉት ይጠብቁናል፡፡ ግንቦት ለደታ ነዋ፤ (ግንቦታ ሃያ አላልኩህም፤ እሱን ፊት-በር ሳይሆን መቀሌ ፈልገው፡፡) እያወራን ያለው ስለ ቅድስት ድንግል ማርያም ልደት ነው::
በዚህ ዕለት ትምህርት ቤት የሚሄድ ልጅም ሆነ፤ ‹ትምህርት ቤት ሄድ› ብሎ የሚቆጣ ወላጅ የለም::
ገና ሰማዩ ወገግ ሲል በሜዳው ላይ የ‹ጽዳት ዘመቻ› ሠራዊት ይሰፍራል፡፡ ከምሳ ሰአት በኋላ ሴቶች ለብቻ፣ ወንዶች ለብቻ ጎድጓዳ ሰሃን ይዘን በየቤቱ ለልመና እንዞራለን፡፡ ዱቄት፣ በርበሬ ዘይት፣ ስንዴ፣ ሽንብራ፣ ጨው፣ ውሃ… ሁሉም ያለችውን አራግፎ ሲሰጠን በደስታ ተውጦ ‹ተባረኩ› ከሚል ምርቃት ጋር ነው::
መንደሩ ችግረኛ ቢሆንም፣ በማርያም ልደት ቸር ሆኖ ይውላል፡፡ ብረት ምጣድ፣ ድስት፣ ሰፌድ ከየቤቱ ይመጣል፤ ንፍሮ ይቀቀላል፤ በቂቤና በርበሬ ያበዱ አነባበሮና ቂጣ፣ ጥፍጥናቸው የኤኔሪኮ ኬክን ያስንቃል፤ ቆሎ ይቆላል፤ ፈንዲሻ እንደ ርንችት ይፈነዳል፡፡
የ‹ቦኖ ውሃ› ነዋሪ አንድም ሳይቀር ይጠራል፡፡ በአሉ በአዎቂዎች መርቃት ይጀመራል፡- ‹ወላዲት አምላክ ታሳድጋችሁ›፣ አዛኝቱ የትምህርታችሁን ብርሃን ትግለጽላችሁ›፣ ‹ድንግል ማርያም ትባርካችሁ›…. ምርቃቱ ይደራል፡፡ እነርሱ የተዘጋጀውን ከቀማመሱ በኋላ ወደ የቤታቸው ሲገቡ እኛ ምሽቱን ገፋ አድርገን አንዴ እየዘመርን፣ መልሰን እየዘፈንን በደስታና በሳቅ እናከብረዋለን፡፡
ይህንን ተናፋቂ ቀን እንደ ቡሄና አዲስ አመት ከህይወታችን ጋር አስተሳስረን፣ ትዝታን አስቀርተን እናከብረዋለን:: ግንቦታ ልደታ፣ በግንቦታ ሃያ ያልተሸፈነች ዕለት!
…ዛሬ እንኳ ይሄ ታሪክ ሆኗል፡፡ አላሙዲን የአካባቢውን ነዋሪ አፈናቅሎ፣ ‹ሻራተን› የሚባል ምግብና መኝታ ቤት ከፍቶበታል፡፡ በርግጥ መንደሩ ሙሉ በሙሉ ከፈረሰ አስር አመት ቢሆነው ነው:: የርስቱ ባለቤቶች፣ ሰፈሩን ያቀኑ ነዋሪዎች ከአጥሩ በሩቅ ሲያማትሩ፤ ባራክ ኦባማና ቢል ጌት ደግሞ ይምነሸነሹበታል፡፡ ዲስፖራና ላሜ ቦራ ይፈነጩበታል፡፡
አዲስ አበባ ውለታ ቢስ ናት፡፡ ለከበርቴ እንጂ፣ ለመስራቾቿ ርህራሄ ኖሯት አያውቅም፡፡ ቀሚሷም ለካድሬ እንጂ፣ ለነዋሪ ተግልቦ አላየሁም፡፡ ለነገሩ ለእቴጌ ጣይቲ ያልሆነች፣ ለእኛማ…
ዕድሜ ለኢሕአዴግ¡ ነባር ነባር ነዋሪዎች በግዴታ ከማኀበራዊ መስተጋብራቸው ተፈናቅለው፣ ገሚሶ እንደ ጦጣ ኮንደምንየም ላይ ተንጠላጥሏል፤ ገሚሱ ምትክ የቀበሌ ቤት ተሰጥቶት እንደ ጥንታውያኑ የአይሁድ ዘር በየቦታው ተበትኗል፡፡ የሚያሰባስበውን ቴውድሮ ዊልዞር ይናፍቃል፤ ከሲውዘርላንድ ሳይሆን፤ ከፊትበር ላንድ፡፡
ሃሃሃ ደሞ ‹ስምነተኛው ንጉሱ እኔ ነኝ› ብለህ እንዳትቀውጠው¡
(ወጉንም ሆነ ፍተላውን በሌላ ጊዜ እመለስበታለሁ)
…መቼም ዛሬ የፊት-በር ሰው ተለውጧል፤ ህፃናቱ ወጣቶች፣ ወጣቶቹ ጎልማሳ ሆነዋል፡፡ ወላጆች በእርጅና ባቡር ከተሳፈሩ ሰንብተዋል::
‹ቢሆንም ቢሆንም› እንዲሉ ሃምሳ አለቃ ገብሩ፤ አድባር የምናከብርበት፣ ትዝታን የምናስቀርበት፣ የአረጋውያን ምርቃትን በኩንታል የምንሸምትበት፣ በማርያም ልደት የምንቆጠርብት ያቺ ልዩ ቀን በሁላችን ልብ ላትሰረዝ ተከትባለች፤ በዕለተ ቀኗ በመንፍስ ባለንበት እንደምታገናኘንም አምናለሁ::
ዛሬም የቅድስት ድንግል ማርያም ቀን ነው፤ ለእናታችን ቅድሲቲቱ ልደት እንኳን አደረሳችሁ!
ከኮሮና ትሰውራችሁ!
አሜን!! ትሰውረን!!!
አዲስ አበባ
ግንቦት 8/2012 ዓ.ም