ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ከኢሕአዴግ (ብልፅግና) ተነጥሎ ትግራይን እያስተዳደረ የሚገኘው ህወሓት ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ ሕግ ሲጥስ የኖረ ድርጅት ከመሆኑ ባሻገር፤ አሁኑም ለአገር ሰላም መደፍረስ ምክንያት የሆኑ ህገወጥ ተግባራትን እየፈጸመ እንደሚገኝ አረና ፓርቲ አስታወቀ።
የአረና ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበርና የመድረክ ሥራ አስፈፃሚ አባል አቶ ጎይቶም ፀጋዬ፤ ህወሓት ከተመሰረተ ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ህግ በመጣስና የጥቂቶችን አምባገነንነት በማንገስ የኖረ ድርጅት በመሆኑ፤ ሕዝቡ የነፃነትን አየር እንዳይተነፍስ ብሎም ከህወሓት ተቃራኒ የቆመውን ሁሉ በጠላትነት ፈርጆ እንዲሰለፍ አስገድደውታል ሲሉ ገልጸዋል።
በድርጅቱ መሃል ሰፋሪ የሚባል ነገር የለም የሚሉት ምክትል ሊቀመንበሩ፤ አመራሮቹን የማይደግፍ ሁሉ በጠላትነት የሚፈረጅበት አሠራር ያለውና አምባገነን አስተሳሰብ የሰፈነበት ፓርቲ እንደሆነ ጠቁመዋል።
በተጨማሪም “አረና ሲቋቋም ትግራይ ከሁለት ፓርቲ በላይ መሸከም አትችልም፤ ክፍፍል ያመጣል ተብሎ ከፍተኛ ተቃውሞ ደርሶብን ነበር” ብለዋል።
“በተለይም የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር (መለስ ዜናዊ) በአንድ መድረክ ላይ፤ አንድ እንስራ ከተሰነጠቀ ዳግመኛ እንደማያለግለው ሁሉ ተጨማሪ ፓርቲ መኖር በትግራይ ህዝብ ዘንድ መከፈፋልን የሚያመጣ ነው በማለት ህዝቡ ፈፅሞ ሌላ አማራጭ እንዳያስብ አድርገውታል” በማለት በህወሓት የተሠራውን የትግራይ ሕዝብን የማታለል ሥራ ያጋለጡት የአረና ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር፤ ይህ አስተሳሰብ ዛሬም ድረስ በከፍተኛ ደረጃ የተንሰራፋ ከመሆኑም በላይ ህገ መንግሥቱ ያስቀመጠውን በነፃነት የመተዳደር መብት የሚጥሱ ተግባራት ጭምር እየተፈፀሙ እንደሚገኝ ይፋ አድርገዋል።
“እንዲህ ዓይነቱ ነገሮች ድርጅቱ ራሱ ያፀደቀውን ህገ መንግሥት እንኳ የማያከብር ስለመሆኑ ትክክለኛ ማሳያ ነው” ያሉት አቶ ጎይቶም፤ የድርጅቱ ኢ-ፍትሃዊ አስተሳሰብ በክልሉ ነግሦ እንዲቆይ በክልሉ ያሉ ሚዲያዎች አስተዋፅኦቸው የጎላ ነው በማለት ያምናሉ::
“በክልል ደረጃም ሆነ በትግራይ ህዝብ ስም የተቋቋሙ አብዛኞቹ ሚዲያዎች፣ ከህወሓት አመራሮች የሚሰጣቸውን ሀሰተኛ ሪፖርቶች በመቀበል የፕሮፖጋንዳ ሥራዎችን በህዝቡ ላይ የሚያሰርፁ ናቸው። የዜናም ሆነ የትንታኔ አቅጣጫዎቻቸው የጋዜጠኝነትን መርሆን ያልተከተሉ፣ በወገንተኝነት ላይ የተመረኮዙ በመሆናቸው ህዝቡን ውዥንብር ውስጥ ከተውታል።” ሲሉ ህወሓት በትግራይ ክልልና ሕዝብ ስም የተቋቋሙ ሚዲያዎችን በሙሉ ለዓላሚው ማስፈጸሚያ እንደተቆጣጠራቸው የገለፁት የአረና ፓርቲ አመራር፤ ሚዲያዎቹ መርጠው የሚያቀርቧቸው ተንታኞችና ባለሙያዎችም የህውሓን አቋም ብቻ የሚያራምዱ፣ ለሕዝብ ጥቅም ያልቆሙ መሆናቸውን ከዋልታ ቲቪ ጋር በነበራቸው ቆይታ ላይ አስረድተዋል ።