ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በመቀለ ከተማ፣ 05 ቀበሌ ተብሎ በሚጠራው ስፍራ ሰብሰብ ብለው የተለያዮ ጉዳዮች ላይ ሲወያዮ የነበሩ ወጣቶችን ለመበተን በፀጥታ ኃይሎች ተደረገው ጥረት ግጭት ቀስቅሶ አንድ ወጣት በፖሊስ አባል ሊገደል መቻሉን የከተማው ፖሊስ ጽሕፈት ቤት አምኗል።
የቫይረሱን ሥርጭት ለመግታት መጠጥ ቤቶች ዝግ መሆናቸውን ተከትሎ፤ ወጣቶች 05 ቀበሌ በሚባለው አካባቢ በአንድ ላይ ተሰባሰበው እየጠጡ ነው የሚል መረጃ እንደደረሰው ያመላከተው ፖሊስ ፤ በጥቆማው መሠረት የፀጥታ ኃይሎች ወደተባለው ሥፍራ ደርሰው፣ ወጣቶቹ እንዲበተኑ ለማድረግ ሲጥሩ፤ በተፈጠረ ግጭት የአንድ ሰው ህይወት ማለፉንና በሁለት ወጣቶች ላይ ጉዳት መድረሱን ገልጿል። በጠፋው ህይወት የተጠረጠረ ፖሊስ በቁጥጥር ሥር መዋሉን የከተማው ፖሊስ አስረድቷል።
የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማስፈጸም የሚንቀሳቀሱ ፖሊሶች በክልሉ ግድያ ሲፈጽሙ የአሁኑ ለመጀመሪያ ጊዜ አይደለም። በከባድ ወንጀልና ዘግናኝ የሆኑ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በሚፈለገው የቀድሞ የደህንነት ሓላፊ የሚመራው የትግራይ የፀጥታ ኃይል አባላት መጋቢት ወር ላይ በትግራይ “ናዕዴር ዓዴት”በሚባለው ወረዳ አንድ ወጣት መግደላቸው አይዘነጋም።
በወቅቱ የጥይት ሰለባ የሆነው ሀጎስ ንጉሥ የተባለው ወጣት የተገደለው ትናንት እንደሞተው ወጣት ፖሊስ መጠጥ ቤት ውስጥ ተሰባስበው የነበሩ ሰዎችን ለመበተን ሲሞክር በተነሳ አለመግባባት ነበር።
መሰብሰብ አይቻልም በሚል የሰው ህይወት በሚጠፋት የትግራይ ክልል ምርጫ ለማካሄድ የሚደረገው እንቅስቃሴ ጋር ፍፁም የተቃረነ መሆኑ አስተያየት ሰጪዎች ተችተውታል።