በኮሮና የምንከፍለው ዋጋ እጅግ አስከፊ መሆኑን ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ገለፁ

በኮሮና የምንከፍለው ዋጋ እጅግ አስከፊ መሆኑን ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ገለፁ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ኢትዮጵያውያን እና በኢትዮጵያ የሚገኙ ሁሉ ምንም ሳይዘናጉ በኮሮና ቫይረስ ዙሪያ የወጡትን መመሪያዎች እንዲተገብሩ አስጠነቀቁ።

” ቫይረሱን ለመከላከል ልንወስዳቸው የሚገቡ ርምጃዎች አካላዊ ርቀትን መጠበቅ፣ እጆችን ቶሎ ቶሎ በመታጠብ በንጽሕና መያዝ፣ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭንብልን በአግባቡ መጠቀም እና ለተወሰነ ጊዜ በቤት የሚቆይበትን ደንብ ተግባራዊ ማድረግን ይጨምራል “ያሉት የብልፅግና መስራችና ሊቀመንበር፤ በከፍተኛ ሁኔታ በቫይረሱ ከተጠቁት ሀገራት ውስጥ አብዛኛዎቹ ያደጉ ሀገራት ናቸው፤ እነዚህ ሀገራትም በፍጥነት እርምጃ ባለመውሰዳቸው እና የቫይረሱን ሥርጭት ለመግታት ፖሊሲዎችን ተግባራዊ ባለማድረጋቸው መፀፀታቸው ፣ ለኢትዮጵያ ትልቅ ትምህርት ነው” ብለዋል፡፡

አካላዊ ርቀትን መጠበቅ፣  በሙሉ ወይም በከፊል ሕዝቡ በቤት እንዲቆይ የማድረግ እርምጃ የቫይረሱ ሥርጭት በአስከፊ ሁኔታ ሳይባባስ ተግባራዊ ከተደረገ፣ ሀገራት የቫይረሱን ሥርጭት ለመግታት እና በጤና አገልግሎት ሥርዓት ላይ የሚደርሰውን ጫና ለመቀነስ እንደሚያስችል በፌስ ቡክ ገፃቸው ያሰፈሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህ ርምጃ ኢኮኖሚን እንደሚጎዳ ቢጎዳም፣ የከፋ ጉዳት ሳይደርስ ሥርጭቱን ለመቀልበስ  ግን እጅግ አስፈላጊ ነው ሲሉም መክረዋል፡፡

በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የኮቪድ-19 ተጠቂ ከተገኘ ጀምሮ እስካሁን 317 ሰዎች በቫይረሱ መጠቃታቸውን ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሌሎች ሀገራት ጋር ሲነጻጸር ቁጥሩ አነስተኛ ቢሆንም፥ ቀስ በቀስ እያሻቀበ ይገኛል ብለዋል፡፡

የቫይረሱ በሀገራችን መገኘት በታወቀበት ሰሞን የሕዝቡ ምላሽ አዎንታዊና ቫይረሱን ለመከላከል የሚረዳ ነበር በማለት ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ፤”ብዙ ዜጎቻቸው ሕይወት በቫይረሱ ከተቀጠፈባቸው፣ የጤና አገልግሎት ዘርፋቸው ከተናጋባቸው እና ኢኮኖሚያቸው በከፍተኛ ሁኔታ ከተቃወሰባቸው ሀገራት ስሕተት ለመማር ካልቻልን የምንከፍለው ዋጋ እጅግ አስከፊ ይሆናል” በማለት ኢትዮጵያውያን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ተማፅነዋል ።

LEAVE A REPLY