ውድ የሀገራችን ህዝቦች
ክቡራትና ክቡራን
‹‹ብዙዎቹ የፈጠራ ውጤቶች የፈተና ልጆች ናቸው›› ይባላል። የሰው ልጆች ከዛሬው ሥልጣኔያቸው ላይ የደረሱት በየዘመናቱ የተደቀኑባቸውን እንቅፋቶች ለማለፍ እውቀትና ክሎታቸውን በስፋት በመጠቀማቸው የተነሣ እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም። አንዳንድ ሊቃውንት ሲናገሩ ‹‹እኛ ሰዎችን ለዛሬው ክብር ያበቃን አዕምሮ ያለው ፍጡር በመሆናችን እና አዕምሯችንን እንድንጠቀም በሚያስገድዱ ሁኔታዎች ውስጥ በማለፋችን ነው›› ይላሉ። እነዚህ ሁለቱ ባይኖሩ፣ ሁላችንም ከዛፍ ወደ ዛፍ ተንጠላጣይ ሆነን እንቀር እንደነበርም ይናገራሉ።
የሰው ልጆች አዳዲስ ጥበቦችን እንዲፈጥሩና ያሉትንም እንዲያሻሽሉ ከገፏቸው ምክንያቶች መካከል አንደኛው በየዘመናቱ የሚከሰቱና የህልውና አደጋ የሚደቅኑ ወረርሽኞች ናቸው። እነዚህ ወረርሽኞች በሰዎች ላይ ካደረሱት መጠነ ሰፊ ጉዳት ባልተናነሰ ወረርሽኙን ለማሸነፍ ሰዎች የፈጠሯቸው ዘዴዎች፣ ቴክኖሎጂዎች፣ ልዩ ልዩ አሠራሮችና የአኗኗር ዘይቤዎች ተያይዘው ይጠቀሳሉ። ለችግር እጅ የማይሰጡ ሰዎች ፈተና ሲገጥማቸው ለመፍጠር ይገደዳሉ። የፈጠራን ፋና ከፈነጠቀው እሳት አንስቶ እስከ ዘመናችን ውስብስብ ኮምፒውተሮች የተፈጠሩት ፈተናዎች ይዘውት የመጡትን እርግማን ትተው ወደ በረከት በሚቀይሩ ጎበዞች ነው።
ኖህ መርከቢቱን ለመስራት የተነሳው ከሚመጣው የጥፋት ውሃ ህዝብን ለማዳን በሚል ነበር፤ ዛሬ መርከብ ለእቃ ማጓጓዣነትና ለመዝናኛነት ይውላል። መከራና ችግር አንዳንድ ደካሞችን አንኮታኩቷቸው ሲያልፍ፣ አንዳንድ አሳቢዎችን ደግሞ ይበልጥ ያጠነክራቸዋል። ያ ጥንካሬያቸውም መልሶ ህዝብን የሚጠቅም ይሆናል። ካወቅንበት ፈጠራ የማሰብና ችግርን ወደ እድል ለመለወጥ የሚደረግ ጥረት እንጂ ሌላ ተአምር እንዳልሆነ እኛ የሰው ልጆች ከታሪካችን በሚገባ ልንማር እንችላለን።
ከዚህ ዘመን በፊት ሲከሰቱ የነበሩ ወረርሽኞች ገሚሶቹ በክትባት የተቀሩትም በህክምና ለመዳን ከመብቃታቸው በፊት የብዙዎችን ህይወት ቀጥፈዋል። ያም ሆኖ የፈጠራ ሰዎች ጭንቅላታቸውን ተጠቅመው ለበሽታዎቹ መድሀኒትና ክትባት ከመስራት ባለፈ ወደፊት ለሚገጥሙን ችግሮች መፍትሔ የምንሰጥበትን ፍጥነት እንድንጨምር የሚያስችለንን በዘመናት የተከማቸ እውቀትና እምቅ አቅማችንን እንድናሳድግ አስችሎናል። ዛሬም የተጋረጠብንን የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ለማለፍ እጅግ የተሻለው መንገድ አንጡራ ሀብታችንንና ዕምቅ ዐቅማችንን ከአዳዲስ ፈጠራዎቻችን ጋር አቀናጅተን መጠቀም ነው። `አንጡራ ሀብት` የሰው ልጅ ከተፈጥሮ ያገኘው የሚታይና የማይታይ ሀብት ሲሆን፣ `ዕምቅ ዐቅም` ደግሞ የሰው ልጅ ያለው አእምሯዊ አቅም ማለት ነው። ይህ አእምሯዊ አቅም የበለጠ በተፈተነ ቁጥር የበለጠ ጥቅም ላይ መዋል የሚችል እየሆነ ይመጣል።
እኛ ኢትዮጵያውያን ከኮቪድ በኋላ እጅግ የተሻለችና ፈተናውን በድል ያለፈች ሀገር ለማየት ከፈለግን እነዚህ ሦስቱን አቅሞቻችንን አጣምረን መጠቀም የግድ ይለናል። እያንዳንዷን ሀብት በሚገባ መፈተሽና ያለ ብክነት መጠቀም አለብን። ሀብትን የሚያበዛው የተገኘው መጠን ብቻ ሳይሆን የአጠቃቀም ችሎታውም እንደሆነ ግልጽ ነው። በተመሳሳይ ያለንን ሀብት በተገቢው ጊዜ፣ ለተገቢው ዓላማ፣ በተገቢው መንገድ መጠቀም እጅግ አስፈላጊ ሲሆን እንደ ሀገር ሀብትን መልሶ ጥቅም ላይ የማወል አቅምና ጥበብን በየጊዜው ማሳደግ ተገቢነቱ አያጠያይቅም። ለዚህም ሕብረተሰባችንን በማስተማርና ንቃተ ህሊናው እንዲዳብር በመትጋት በኩል ሁላችንም ሀላፊነት አለብን። ትልቁ የሰው ልጆች የሀብት ምንጭ አዕምሮ እንደመሆኑ መጠን፣ እውቀት ላይ የተመሰረቱ ሀብቶቻችንን አብዝተን ለመጠቀም ከፍተኛ ትግል ከማድረግ መቦዘን የለብንም።
የማይነጥፈውን የሀብት ምንጭ አዕምሮን ወደ ሀብትነት የምንቀይርበት ዋነኛው መንገድም ፈጠራ ነው። `ፈጠራዎች` ችግር ፈቺ፣ ወጪ ቆጣቢ እና በርካሽ ዋጋ ለብዙዎች ተደራሽ መሆን ሲችሉ ሀገር ከፈጠራዎቹ የምታገኘው ጥቅም በጣም ከፍተኛ ይሆናል። ለዚህም፣ ደግሞ ደጋግሞ ማሰብ በእጅጉ ይጠይቃል። ነገሮችን በተለያዩ አቅጣዎች መመልከት፣ እንደ አዲስ መፈተሽ እና ሳይታክቱ መሞከር የፈጠራ ቁልፎች ናቸው።
ኮቪድ 19`ን ተከላክለን የተሻለች ሀገር ለመገንባት ባለን ሀብት ላይ እውቀትና ፈጠራን አቀናጅተን መጠቀም ይኖርብናል። በዚህ መንገድ ፋታ የማይሰጠውን ወረርሽኝ ፋታ ልንነሣው እንችላለን። በአሁኑ ወቅት፥ በገጠርና በከተማ የሚገኙ ለእርሻ ምቹ የሆኑ መሬቶቻችንን ለምግብ ሰብል ምርት ማዋል አለብን፤ አምራች ኢንዱስትሪውና ሠራተኞቹ ዐቅማቸውን ሁሉ ለተጨማሪ ምርት እንዲያውሉ ማበርታት ይገባናል፤ በግብርና ሥራ ላይ የተሠማሩ አርሶ አደሮችና ባለሞያዎችን ማበረታታት ተገቢ ነው፤ በመጭው ክረምት ያቀድነውን የ5 ቢልዮን ችግኝ ተከላ ወገባችንን አሥረን ማሳካትም ይኖርብናል። በተጨማሪም ዜጎች በቤት ሲቀመጡ ሊያከናውኗቸው የሚገቡ የሞያና የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎችን ከማትጋት በዘለለ የሀገር ፍቅርና የሕዝቦች አንድነትን ማጠናከር አለብን።
በዚህ መልኩ ለወረርሽኙ ስርጭት እድል ሳንፈጥር ለሀገር ግንባታ ከተጋን ያለ ጥርጥር ኮሮናም በቀላሉ ይሸነፋል፤ ሀገራችንም በብልጽግና ጎዳና ትረማመዳለች። ለዚህ ደግሞ የቴክኖሎጂና የኪነ ጥበብ ፈጠራዎች የበለጠ ጉልበት እንደሚሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም። የማኅበረሰቡን አስተሳሰብ የሚያሳድጉና ፈተናን ወደ ዕድል የሚቀይሩ አብሪ ሐሳቦች በተለይ በዚህ ወቅት በእጅጉ ያስፈልጉናል።
ስለሆነም መንግስት በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ የሕዝቡን ኖሮ ለማሻሻል የሚያስችሉ የተለያዩ የቴክኖሎጂና የኪነ ጥበብ ፈጠራ ያሏቸውን ኢትዮጵያውያን ማበረታታት ይሻል። ከዚህ አኳያ፡-
• የገበሬውን ምርታማነት ሊያሻሽሉ የሚችሉ አዳዲስ አሰራርና ቴክኖሎጂዎች፤
• የከተማ ግብርናን የሚያበረታቱ፣ የሚያሳልጡና ውጤታማ የሚያደርጉ ልዩ ልዩ ዘዴዎች፤
• የፋብሪካ ምርታማንትን የሚያሳድጉ የተመረጡ መንገዶችና አሰራሮች፤
• ዜጎቻችን በቤት ውስጥ ሲቀመጡ የንባብ ፍላጎታቸውና ችሎታቸው እንዲዳብር የሚያደርጉ ፈጠራዎች፤
• በቤት የሚቀመጡ አረጋውያን፣ ጎልማሶች፣ ወጣቶችና ሕጻናት በቀላሉና ወደዋቸው ሊያከናውኗቸው የሚችሉ ማራኪ የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎች፤
• ሕዝቡን ለፈጠራ፣ ለአዳዲስ ሙከራዎች እና የቴክኒክ እውቀቱን ከፍ ለማድረግ የሚረዱ ድርሰቶች፣ ሙዚቃዎች፣ ሥዕሎች፣ አጫጭር ድራማዎችና አጫጭር ፊልሞች፤ እንዲሁም
• የሕዝቦቻችንን አንድነት፣ የእርስ በርስ ትውውቅና የሀገር ፍቅር ስሜት የሚያሳድጉ ጥበቦችና ፈጠራዎች ያሏችሁ ሳትዘገዩ አሁኑኑ አውጧቸው።
በዚህ መልኩ እስከ መስከረም ድረስ በተለያዩ ሚዲያዎችና መድረኮች የሚቀርቡ የተሻሉ የፈጠራ ውጤቶችን መርጦ በቀጣዩ ዓመት ለመሸለም በመንግስት በኩል ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ ነው። ስለሆነም ፈጠራዎቻችሁን ያለማቋረጥ በተለያዩ መንገዶች ለሕዝብ አቅርቧቸው። ሥራዎቻችሁን በዋነኞቹና በማህበራዊ ሚዲያዎች አማካኝነት የማስተዋወቂያው ትክክለኛ ጊዜ አሁን ነው። ይሄን ተከታትሎ የሚይዝ፣ ከየሚዲያው ወስዶ የሚመዘግብና ለሽልማት የሚያጭ አካል መንግሥት በቅርቡ አቋቁሞ የሚያሳውቅ ይሆናል።
አመሰግናለሁ!
ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትሩር!!
ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ይባርክ!