ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡- ለዓመታት ጣና ሐይቅን የወረረው የእንቦጭ አረም ከሰሞኑ ግዛቱን እያሰፋ መሆኑ በመነገር ላይ ነው፡፡
የእምቦጭ አረም ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ በሀገር ውስጥ በተሠሩ እና ከውጭ በገቡ ማሽኖች ከጣና ሀይቅ ላይ አረሙን ለማጥፋት ጥረት ተደርጓል ቢባልም ፤ በተለይ ባለፉት አስራ ሁለት ወራት አረሙን የማጥፋት ዘመቻው በእጅጉ መቀዛቀዙ አይዘነጋም ።
መጥፎው አረም በፍጥነት የመስፋፋት ባህሪይ ያለው መሆኑን ተከትሎ በተለይም በለውጡ ማግስት (በ2010 መገባደጃ) በሀገር ውስጥና በውጭ የሚገኙ ባለሀብቶች ከፍተኛ የሆነ የገንዘብ ድጋፍ ቢያደርጉም ሥራው በተገቢ መንገድ እንዳልተሠራ ፤ በተለይም የአማራ ክልል መንግሥት ከእምቦጭ ይልቅ ለፖለቲካ ጉዳዮች ቅድሚያ መሰጠቱና የፌደራል መንግሥቱም በተመሳሳይ ሐሳብ መደመጡ የጥፋቱን መጠን ጨምሮታል ።
ከተለያየ አቅጣጫ እንዲህ ዓይነት ትችቶች ቢቀርቡም ፤ ጣና ሀይቅን የመጠበቅ ሓላፊነት የተጣለበት ኤጀንሲ በበኩሉ ፣ አረሙ ተስፋፍቶባቸው ከነበሩ 30 ቀበሌዎች 25ቱ ከሞላ ጎደል ነፃ ሆነዋል በማለት አስተባብሏል፡
ሥራዬን በአግባቡ እያከናወንኩ ነው የሚለው ኤጀንሲው፤ ሐይቁን ከእምቦጭ ለማፅዳት ከተሰበሰበው ገንዘብ 40 ሚሊዮን ብሩ ገና ሥራ ላይ አለመዋሉንም ገልጿል፡፡