ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡- ኢትዮጵያ ውስጥ የኮቪድ 19 ቫይረስ ከተገኘባቸው 365 ሰዎች ውስጥ 228 የሚሆኑት በአዲስ አበባ እንደሚገኙ የጤና ሚኒስቴር ገለፀ፡፡
በተሰበሰበው ዳታ መሠረት የልደታ ክ/ከተማ 40 በመቶ የሚሆነውን ቫይረሱ ያለባቸውን ሰዎች ቁጥር ሲይዝ፣ አዲስ ከተማ ክፍለከተማ በሁለተኛነት ድርሻውን መያዙን ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ አስታውቀዋል።
አሁን ያለው አኃዛዊ መረጃ ቫይረሱ በአዲስ አበባ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ መምጣቱን የሚያመላክት እንደሆነ ፣የውጭ ሀገር የጉዞ ታሪክ የሌላቸው፣ እንዲሁም ቫይረሱ ካለበት ሰው ጋር ግንኙነት ሳይኖራቸው በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 16 በመቶ መድረሱም በከተማዋ በሽታው አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ያረጋግጣል ብለዋል ሚኒስትሯ፡፡
የቫይሱን ስርጭት ለመቆጣጠርም ከቫይረሱ ጋር ንክኪ ያላቸውን ሰዎች ቅኝት የማድረግ ሥራ ዋነኛ ተግባር መሆኑን የገለጹት ደግሞ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት ዳይሬክተር ዶ/ር ኤባ አባተ በበኩላቸው ፤ በልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 በተደረገ ቅኝት ከቫይረሱ ጋር ንክኪ ከነበረው አንድ ሰው ጋር ንክኪ የነበራቸው 32 ግለሰቦች ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል ሲሉ በሕዝብ ዘንድ መመሪያዎችን ተግባራዊ ያለማድረግ ችግር መኖሩን አስታውቀዋል፡፡
በተመሳሳይ በወረዳው በሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ በተደረገ ድንገተኛ ምርመራ 40 የሕግ ታራሚዎች ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል፡፡ የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ እስካሁን 62 ሺህ 300 የላብራቶሪ ምርመራ የተደረገ ሲሆን፤ ካለፉት 2 ወራት ይበልጥ በሁለት ሳምንት ውስጥ የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር 63 በመቶ ድርሻ እንዳለው ገልፀዋል፡፡