ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡- ባለፉት 24 ሰዐታት ለ3 ሺኅ 460 ሰዎች በተደረገ የላቦራቶሪ ምርመራ 24 ሰዎች የኮሮና ቫይረስ እንደተገኘባቸው የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ይፋ አድርገዋል።
በቫይረሱ ከተያዙት ውስጥ 18 ወንድ፣ ስድስቱ ደግሞ ሴት ሲሆኑ፤ ሁሉም ኢትዮጵያውያን መሆናቸው ተረጋግጧል። ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች እድሜያቸው ከ4 እስከ 58 ዓመት የሚገኙ እንደሆኑም መግለጫው ያሳያል።
ዛሬ በኮቪድ 19 ቫይረስ ግኝት መዝገብ ውስጥ ከሰፈሩት 24 ሰዎች መሀል ዘጠኝ ከአዲስ አበባ፣ ሠባት ከትግራይ ክልል፣እንዲሁም ስምንት ሰዎች በአማራ ክልል መተማ ለይቶ ማቆያ ያሉ ናቸው ያለው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር መግለጫ ፤ ከእነዚህ ውስጥ 12ቱ የውጭ ሀገር የጉዞ ታሪክ ያላቸው ሲሆኑ፣ ስምንቱ ደግሞ ቫይረሱ ከተገኘበት ሰው ጋር ግንኙነት የነበራቸው መሆናቸውን አረጋግጧል።
ቀሪዎቹ አራት ሰዎች፤ የውጭ ሀገር የጉዞ ታሪክም ሆነ ቫይረሱ ከተገኘበት ሰው ጋር ግንኙነት የሌላቸው መሆኑን ያመላከቱት ሚኒስትሯ፤ ከበሽታው አዲስ ያገገሙ ሁለትሰዎች መኖራቸውን ተከትሎ እስካሁን በጠቅላላ ከቫይረሱ ያገገሙ ሰዎች ቁጥር 122 (አንድ መቶ ሀያ ሁለት) ደርሷል ብለዋል።