ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡- በኤል ቲቪ የተለያዮ ታዋቂ የፖለቲካ ሰዎችንና ምሁራንን ቃለመጠይቅ በማድረግ የምትታወቀውና በምትመርጣቸው እንግዶችና ጥያቄዎቿ በጽንፈኛ ብሔርተኝነት የምትተቸው ቤተልሔም ታፈሰ፤ የምትሠራበትን ቴሌቪዥን ጣቢያ ለመልቀቅ ደብዳቤ ማስገባቷ ተሰማ።
እንደ ታማኝ ዜና ምንጮቻችን ከሆነ ቤተልሔም ለLTV ባቀረበችው መልቀቂያ ላይ በሥራዋ ላይ ውስጣዊ ጫና እየደረሰባት መሆኑን ምክንያት አድርጋለች። “በተለያዩ መንገዶች ከውጭ እየደረሰብኝ ያለውን ፈተና ተቋቁሜ ብሠራም፣ ከውስጥ እየገጠመኝ ያለውን ጫና ከዚህ በላይ ታግሼ ለመሥራት ስለማያስችለኝ፣ ከዛሬ ጀምሮ ሥራዬን በገዛ ፍቃዴ ለቅቂያለሁ” በማለት የመልቀቂያ ደብዳቤ ማስገባቷ ተሰምቷል።
ቤተልሔም ታፈሰ በዚህ ሳምንት ከኦፌኮ ም/ክ ሊቀመንበር ፖለቲከኛ አቶ በቀለ ገርባ ጋር ልታደርገው የነበረው ቃለ መጠይቅ ከእሷ ፍላጎት ውጪ መሰረዙ ሥራዋን ለመልቀቋ ምክንያት እንደሆነ ለኤል ቲቪ ቅርበት ያላቸው የኢትዮጵያ ነገ ምንጮች ተናግረዋል ።
በጃዋር መሐመድና በጽንፈኛ የኦሮሞ ብሔርተኞች ዙሪያ ያሉ የፖለቲካና የሃይማኖት ሰዎችን በመጋበዝ የብሔር ፖለቲካን በማራገብ ረገድ ዓይነተኛ ሚና ተጫውታለች በማለት የምትተቸው ቤተልሔም በዚህ ሳምንት ከአቶ በቀለ ገርባ ጋር በምርጫና ከመስከረም 30 በኋላ መንግሥት የለም በሚለው ዙሪያ ሰፋ ያለ ፕሮግራም ለመሥራት አቅዳ ነበር ።
ይህ እቅዷ የከሸፈባት ቤተልሔም ታፈሰ በዚህ ምክንያት የምትሠራበትን ጣቢያ ለመልቀቅ ደብዳቤ ያስገባች መሆኑን የጠቆሙት ምንጮቻችን ጣቢያው እስካሁን ድረስ ለጥያቄዋ ምላሽ እንዳልሰጣት ገልጸዋል። ቤተልሔም ታፈሰ በጥያቄዋ መሠረት ኤል ቲቪን የምትለቅ ከሆነ አንድ አካባቢ ያደጉትና የቅርብ ወዳጇ፣ እንዲሁም በእጅጉ የምታደንቀው የጃዋር መሐመድ ንብረት የሆነው ኦ ኤም ኤን ቴሌቪዥን ልትገባ እንደምትችል በቅርብ የሚያውቋት ግምታቸውን ከወዲሁ አስቀምጠዋል ።