ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በኢትዮጵያ ባለፉት 24 ሰዐታት ውስጥ ለ3747 (ሦስት ሺኅ ሠባት መቶ ዐርባ ሠባት) ሰዎች በተደረገ የላብራቶሪ ምርመራ፤ ዘጠኝ ሰዎች ላይ የኮሮና ቫይረስ መገኘቱን የጤና ሚኒስቴር ሚኒስቴሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ገለፁ፡፡
ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው 8 ወንድ እና 1 ሴት ኢትዮጵያዊያን ሲሆኑ ፤ ከ 20 እስከ 49 ዓመት የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ናቸው ተብሏል፡፡
ከዘጠኙ ሰዎች ውስጥ ሦስቱ ሰዎች ከአዲስ አበባ ሲሆኑ ፣2ቱ (በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር ግንኙነት የነበራቸው) እንዲሁም 1 ሰው (የውጪ ሀገር የጉዞ ታሪክ ያለው) ሆኖ ተመዝግቧል። ሁለት ሰዎች ከአፋር ክልል (የውጪ ሀገር የጉዞ ታሪክ ያላቸው እና በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር ግንኙነት የሌላቸው)፣ 1 ሰው ከሶማሊያ ክልል (የውጪ ሀገር የጉዞ ታሪክ ያለው እና ጅግጅጋ ለይቶ ማቆያ ያለ)፣ 1 ሰው ከትግራይ ክልል (የውጪ ሀገር የጉዞ ታሪክ ያለው እና በማይካድራ ለይቶ ማቆያ ያለ)፣ እንዲሁም 2 ሰዎች ከአማራ ክልል (የውጪ ሀገር የጉዞ ታሪክ ያላቸው እና መተማ ለይቶ ማቆያ ያሉ የዛሬው የኮቪድ 19 ቫይረስ ተጠቂዎች እንደሆኑ ታውቋል፡፡
በዚህ መሠረት እስካሁን በአጠቃላይ በኢትዮጵያ በቫይረሱ የተያዙትን ሰዎች ቁጥር 398 ደርሷል፡፡ በሌላ በኩልበትናንትናው እለት አንድ ሰው ከአዲስ አበባ ከበሽታው ማገገሙን ተከትሎ በኢትዮጵያ በአጠቃላይ ከበሽታው ያገገሙ ሰዎች 123 መድረሱን ዶክተር ሊያ ታደሰ ይፋ አድርገዋል፡፡