በጉጂ ዞን የኦነግ ወታደር በነበሩ ታጣቂዎች 12  የኦሮሚያ ፖሊስ አባላት ተገደሉ

በጉጂ ዞን የኦነግ ወታደር በነበሩ ታጣቂዎች 12  የኦሮሚያ ፖሊስ አባላት ተገደሉ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– በጉጂ ዞን አስራ ሁለት የኦሮሚያ ክልል ልዩ ፖሊስ አባላት በታጣቂዎች መገደላቸውን የዞኑ ባለስልጣን አስታወቁ። የጉጂ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ማሊቻ ዲቃ እንደተናገሩት ከሆነ፤ በግጭቱ በሰው ሕይወት እና በንብረት ላይ ጉዳት እየደረሰ መሆኑን ለቢቢሲ ገልፀዋል።

በታጣቂዎቹና በክልሉ ልዩ ኃይል አባላት መካከል ከሁለት ሳምንት በፊት በነበረ ግጭት 12ቱ የኦሮሚያ ልዩ ፖሊስ አባላት በታጣቂዎቹ መገደላቸውን ሓላፊው ተናግረዋል ።

በደቡብ አሮሚያ ጉጂ ዞን በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች እና በቀድሞ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) አባል የነበሩና በአሁን ወቅት በጫካ ውስጥ እየተንቀሳቀሱ ባሉ ታጣቂዎች መካከል ግጭት እየተካሄደ መሆኑን ታማኝ ምንጮች አረጋግጠዋል። “በጉሚ ኤልደሎ ወረዳ ግጭት ተከስቶ 12 የኦሮሚያ የልዩ ኃይል የፖሊስ አባላት ተገድለዋል። የሞቱት ቁጥራቸው ስንት እንደሆኑ ባናውቅም ከታጣቂዎቹም የተገደሉ አሉ” ያሉት አቶ ማሊቻ ዲቃ ጉዳቱ በሁለቱም በኩል በከፍተኛ ሁኔታ ደርሷል ብለዋል ።

በጉጂ ዞን ታጥቆ የሚንቀሳቀሰው ኃይል በአካባቢው ነዋሪዎች የዕለት ተዕለት ኑሮ ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ጫና እያሳደረ እንደሚገኝ የጠቆሙት አቶ ማሊቻ “የአካባቢው ነዋሪዎች የእለት ከእለት ሕይወታቸውን መቀጠል አልቻሉም። ገበሬው ማረስ አልቻለም፤ አርብቶ አደሩም ከብቱን ማርባት አልቻለም። የመንግሥት ደጋፊ ናችሁ እየተባሉ ታፍነው የተወሰዱ ሰዎችም አሉ። በስልክ ማስፈራሪያ የደረሳቸውም አሉ” ሲሉ ሁኔታውን አሳይተዋል።

የአካባቢውን ሰላም ለማስከበር በዞኑ የአገር መከላከያ ሠራዊት፣ የኦሮሚያ ልዩ ኃይልና መደበኛ ፖሊሶች ተሰማርተዋል ።በተለይ በዞኑ በሚገኙት ሠባ በሩ፣ በጎሮ ዶላ እና ሻኪሶ ወረዳ ግጭቶች እንደቀጠሉ የሚናገሩት ምክትል አስተዳዳሪው፤ “በሁለቱም በኩል ሰው ይሞታል። በታጣቂዎች በኩል ምን ያክል ሰው እንደሞተ ግን የምናውቀው ነገር የለም” ብለዋል ።

LEAVE A REPLY