በግድቡ ዙርያ የኢትዮጵያ እና የግብፅ አካሄድ! || ኤልያስ መሰረት

በግድቡ ዙርያ የኢትዮጵያ እና የግብፅ አካሄድ! || ኤልያስ መሰረት

ከሳምንታት በፊት አንድ ከፍተኛ የሀገራችን ዲፕሎማት እንዲህ ብለውኝ ነበር: “አሜሪካ በዚህ በያዝነው የፈረንጆች አመት ልታሳካቸው ያቀደቻቸው አምስት ዋና የውጭ ጉዳይ አጀንዳዎች አሏት። እነርሱም ከኢራን፣ ከሰሜን ኮርያ፣ ከቻይና፣ ከአፍጋኒስታን እንዲሁም ከግብፅ ጋር ይገናኛሉ። ያው፣ የግብፅ ጉዳይ የተባለው በህዳሴ ግድብ ዙርያ ያለውን የድርድር አጀንዳ ቶሎ መቋጨት እና የፍልስጤም የሰላም ሂደትን በግብፅ ድጋፍ ማስቀጠል ነው።”

አሜሪካ ፕሬዝደንታዊ ምርጫዋን ልታካሂድ ስድስት ወር ብቻ ይቀራታል። የፕሬዝደንት ዶናልድ ትረምፕ አስተዳደር አካሄድ የተመቸው የግብፅ መንግስት ከዚህ ምርጫ በፊት ዋሽንግተን ዲሲ ውስጥ በግድቡ ዙርያ ቶሎ ስምምነት ላይ ለመድረስ ቋምጦ ነበር፣ ምክንያቱ ደግሞ የዴሞክራት እጪ የሆኑት ጆ ባይደን ምርጫውን ቢያሸንፉ ይህን መሰል ድጋፍ ወደፊት እንደማያገኙ ስለገመቱ ሊሆን እንደሚችል ማሰብ ይቻላል።

አሜሪካ ለግብፅ ልትወግን የምትችልባቸው ሶስት ዋና ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላሉ። በመጀመርያ አሜሪካ የእስራኤል-ፍልስጤም የአመታት ፍጥጫን በጃሬድ ኩሽነር በኩል ለመፍታት እየሞከረች ስለሆነ በአረቡ አለም ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር ላላት እና ተፅእኖ መፍጠር ለምትችለው ግብፅ በዚህ ግድብ ዙርያ ውለታ በመዋል ድጋፏን ትፈልጋለች። ሲቀጥል ግብፅ ያላት አጠቃላይ የጂኦ-ፖለቲካል ጥቅም ለአሜሪካ ከኢትዮጵያ ይልቅ እጅግ ከፍ ያለ ነው፣ በተለይ የሱዊዝ ካናል መገኛ ሀገር መሆኗ እና አሜሪካ በአካባቢው ለምታደርገው ማኛውም እንቅስቃሴ ከፍተኛ ድጋፍ ይሆናል። በመጨረሻም በግብፅ እና አሜሪካ ወታደራዊ ተቋማት መሀል ለ30 አመታት የቆየው ግንኙነት ጠንካራ እንደሆነ ይሰማል፣ ይህም ሁለቱም ሀገራት ከእስራኤል ጋር ጥሩ ግንኙነት ስላላቸው እና ኢራንን እንደ የጋራ ጠላት የማየታቸው ጉዳይ ሊሆን ይችላል።

በቅርቡ ኢትዮጵያ የዋሽንግተኑን ሂደት “ፍትሀዊነት የጎደለው” ብላ ጥላ መውጣቷ የግብፅን ሀሳብ አምክኖታል። ለዚህም ይመስላል የግብፅ ዲፕሎማቶች ከብራሰልስ እስከ ቡጁምቡራ፣ ከኒውዮርክ እስከ ናይሮቢ እየተጓዙ ለሀገራት እና ለአለም አቀፍ ድርጅቶች አቤት እያሉ የሚገኙት።

ከዚህ ውጪ በሀገሪቱ ያሉ የግልም ሆኑ የመንግስት የሚድያ ተቋማት በጉዳዩ ዙርያ (አንዳንዴ የውሸት መረጃ የሚረጩትን ጨምሮ) በርካታ ዘገባዎችን እየሰሩ ለህዝባቸው እያደረሱ ነው። ይህም በህዝቡ ዘንድ “ውሀ ልትጠማ ነው፣ ሊርብህ ነው” የሚል መልእክት የሚያስተላልፉትን ይጨምራል። ለዚህ የሚድያ ዘመቻ ስራ አዲስ አበባ በሚገኘው የግብፅ ኤምባሲ ይሰሩ የነበሩ ዲፕሎማቶችን፣ ታዋቂ ግለሰቦችን እንዲሁም የሚድያ ሰዎችን እየተጠቀሙ ነው።

ወደ እኛ መለስ ስንል የውስጥ የፖለቲካ ሽኩቻ እና የኮሮና ቫይረስ መረጃ በብዛት ሚድያውን አጥለቅልቆታል። ከስንት አንዴ በግድቡ ዙርያ መረጃ ሲኖር እርሱም ብዙ ሳይሰማ በሌላ ጉዳይ ቶሎ ይዋጣል።

በጉዳዩ ላይ እውቀት ያላቸው ብቻ ሳይሆን ለሌላ ሀገር ጭምር የሚተርፉ ናቸው የሚባሉት የውሀ እና ግድብ ኤክስፐርቶቻችን ብዙ ነገር ሲሉ አይሰማም፣ ሚድያዎችን ለማናገርም ብዙም አይፈልጉም። የግድቡ ፕሮጀክት ብዙ አመት እየተጓተተ ስለመጣ ሰለቻቸው መሰለኝ በተለይ የግል ሚድያዎች እንደ ግብፅ አቻዎቻቸው መረጃዎችን በተደጋጋሚ እና በሀገራዊ መንፈስ ሲያቀርቡ ብዙ አይታይም። ውጭ ጉዳይ አካባቢ ጥሩ የመንቀሳቀስ ነገር ይታያል፣ ግን ልምድ ያላቸውን ዲፕሎማቶች ወደፊት በማምጣት ስራ ሊሰራ እንደሚገባ ሲነገር እንሰማለን።

ያም ሆኖ እንደ ኡመር ረዲ እና መሀመድ አል-አሩሲ ያሉ ወጣት ተንታኞች በተለይ በአረብኛ ቋንቋ በሚተላለፉ የውጭ ሀገር ቻናሎች ላይ በመሳተፍ ድምፅ ማሰማት መጀመራቸው አበረታች ነው። በጉዳዩ ዙርያ በቅርቡ መፅሀፍ ያሳተመው ጋዜጠኛ ስላባት ማናዬም ሊመሰገን ይገባል።

LEAVE A REPLY