ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የባህዳርና አካባቢዋ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዛሬ በዋለው ችሎት በቀድሞው የብአዴንና ኢሕአዴግ ከፍተኛ አመራር በነበሩት አቶ ታደሰ ካሳ (ጥንቅሹ) ላይ በሌላ የክስ መዝገብ 8 ዓመት ከአምስት ወር ጽኑ እስራትና በ20 ሺህ ብር መቅጣቱ ተሰማ።
ችሎቱ ቅጣቱን ያሳለፈው ጥረት ኮርፖሬትን በዋና ሥራ አስፈፃሚነት አቶ ታደሰ ካሳ ይመራ በነበረበት ወቅት፤ ከሌሎች ጋር በመተባበር ሥራን በማያመች መንገድ መርተዋል በሚልና በተለያዩ የሙስና ክሶች ጥፋተኛ ሆነው ስላገኛቸው ነው።
በእነታደሰ ካሳ የክስ መዝገብ ጉዳያቸው ሲታዩ የነበሩ ተከሳሾችም ዛሬ ውሳኔ ተሰጥቷቸዋል።
በዚሁ መዝገብ ሥር የተዘረዘሩ ሌሎች ተከሳሾች፣ ከሁለት ዓመት እስከ ሦስት ዓመት ከሠባት ወር የሚደርስ እስርና ከአራት ሺኅ እስከ 10 ሺኅ የሚደርስ የገንዘብ ቅጣትተጥሎባቸዋል፡፡ ይሁን እንጂ ከአቶ ታደሰ ካሳ ውጭ ያሉት ተከሳሾች 50 ሺኅ ብር ዋስትና አስይዘው በሁለት ዓመት ገደብ እንዲለቀቁ ፍርድ ቤቱ አዝዟል፡፡
አቶ ታደሰ ካሳ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሚያዚያ 30/2012 ዓ/ም በዋለው ችሎት ከአቶ በረከት ስምኦን ጋር በተመሰረተባቸው ተመሳሳይ የሙስና ክስ 8 ዓመት ጽኑ እስራትና 15 ሺህ ብር መቀጣቱ አይዘነጋም። ከትናንት በስቲያ በነበረው ችሎት በዚሁ መዝገብ ሥር ተከስሰው የነበሩት አቶ ምትኩ በየነ እና ሀጂ ሁሴን አህመድ በነፃ መለቀቃቸውም ተሰምቷል፡፡