ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በከፍተኛ ችግር ውስጥ የሚገኙትና ወደ አገራቸው መመለስ የሚፈልጉ በሌባኖስ (ቤይሩት) የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ለበረራ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከፍተኛ ገንዘብ እየጠየቀን ነው አሉ።
አየር መንገዱ በሊባኖስ የመኖሪያ ፍቃድ ያላቸው ኢትዮጵያውያን ከቤይሩት ወደ አዲስ አበባ ለሚደረግ አንድ በረራ 680 ዶላር እንዲከፍሉ ፣ የመኖሪያ ፍቃድ የሌላቸው ደግሞ በቆንስላው በኩል ተመዝግበው 580 ዶላር እንዲከፍሉ መጠየቃቸውን ተናግረዋል።
ትነበብ በኃይሉ የተሰኘችና ብዙ ዓመታት የቆየች ኢትዮጵያዊ ፤ “የምግብ እርዳታ የሚቀበሉ ልጆች እንዴት አድርገው ነው 580 እና 680 ዶላር መክፈል የሚችሉት? በአገሪቱ የጠፋ ዶላር ከየት ነው የሚመጣው? ዋጋው በጣም የበዛ ነው ፤ ከዚህ ቀደም ከቤይሩት ወደ አዲስ አበባ ለሚደግ በረራ ተወደደ ከተባለ 350 ዶላር ይከፈል ነበር ፣ በዚሀ አስቸጋሪ ወቅት ይህን ያክል ገንዘብ ከየትም ሊመጣ አይችልም። አይደለም እኛ የሌባኖስ ዜጎች እራሳቸው ዶላር ቸግሯቸዋል። 580 ዶላር ለማግኘት እና ኤምባሲ ለመመዝገብ ገላቸውን እስከ መሸጠ የደረሱ አሉ” በማለት ሀቁን በመግለፅ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዚህ የጭንቅ ወቅት በዜጎቹ ላይ ለትርፍ የሚያደርገውን ሩጫ ተችታለች።
በሊባኖስ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአካባቢ ማናጀር የሆኑት አቶ ዳንኤል ጽጌ በበኩላቸው የትኬት ዋጋው ከተለመደው ውጪ ከፍ ያለበት ምክንያት፤ አየር መንገዱ ከቤይሩት-አዲስ አበባ በሚያደርገው በረራ ትርፍ እያገኘ ባለመሆኑ መሆኑን ለቢቢሲ ገልጸዋል።
“ይህ የንግድ በረራ አይደለም። ይህን የትኬት ዋጋ ያወጣነው ወጪያችንን እንዲሸፍን ብቻ ነው። ምንም አይነት ገቢ አያስገኝም። ወጪውን እንዲሸፍን ብቻ ነው ፤ ዝርዝር ስሌት አለን። ከዚህ ቀደም ከቤይሩት ተነስተው በአዲስ አበባ በኩል አድረግው ወደ ሌሎች አገራት የሚሄዱተሳፋሪዎችም በዚህ በረራ ላይ ይኖሩ ነበር። 3ሺኅእና 4ሺኅ ዶላር ድረስም የሚከፍሉ አሉ። አሁን ግን ይህ የለም። አሁን ላይ የምናሳፍረው መንገደኞች በቁጥር ጥቂት ናቸው። በዚያ ላይ ወደ አዲስ አበባ ብቻ የሚሄዱ ናቸው” በማለት በቀደመው ዋጋ ኢትዮጵያውያኑን ብቻ በቀጥታ ማመላለስ አየር መንገዱን እንደማያዋጣው አብራርተዋል።