ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በአንድ ሳምንት ውስጥ ግምታዊ ዋጋቸው ከ23 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር በላይ የሚሆኑ የኮንትሮባንድ ዕቃዎችና የጦር መሳሪያዎች በቁጥጥር ሥር ዋሉ ።
የተያዙት የኮንሮባንድ ዕቃዎች በህገ-ወጥ መንገድና በቱሪስት ስም የገቡ ተሽከርካሪዎች፣ የተሽከርካሪዎች መለዋወጫ፣ አዳዲስ እና አሮጌ አልባሳት፣ ኤለክትሮኒክስ፣ ጊዜው ያለፈባቸው መድኃኒቶች፣ ምግብና የምግብ ነክ ቁሳቁሶች፣ ሞባይሎች፣ ጫት፣ ሲጋራ፣ አደገኛ እፅና ሺሻ መሆናቸውን የገቢዎች ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
ብዛቱ 14 ሺኅ 474 የቱርክ ሸጉጥ ጥይት እና 3 ስታር ሽጉጥ ከመተማ ወደ አዲስ አበባ በመጓዝ ላይ ሳለ ሰርባ ኬላ ፍተሻ ላይ ከፌደራል ፖሊስ አባላትና ከክልሉ ፀጥታ አካላት ጋር በቅንጅት በተሠራው ሥራ ከ2 ተጠርጣሪዎች ጋር ከኅብረተሰቡ በደረሰ ጥቆማ ሊያዝ ችሏል።
ድሬዳዋ፣ አዋሽ፣ ጅግጅጋ፣ ሀዋሳ፣ ሞያሌ፣ መቀሌ፣ አዳማ፣ አዲስ አበባ እና ሌሎች የጉምሩክ ኬላና መቆጣጠሪያ ጣቢዎች የኮንትሮባንድ ዕቃዎቹ የተያዙባቸው ቦታዎች እንደሆኑም የሚኒስትር መ/ቤቱ መግለጫ ያሳያል፡፡
በተጨማሪም በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ በቦሌ አየር መንገድ እና ሞጆ ጉምሩክ መቆጣጠሪያ ጣቢያ በኩል የሚገቡት የዕቃዎችን ሰነድና ንግድ በማጭበርበር ለማስተላለፍ ቢሞክሩም፣ በተደረገው ጥብቅ ፍተሻ ከ4 ነጥብ 6 ሚሊየን ብር በላይ ለመንግሥት ተጨማሪ ታክስና ግብር እንዲከፈል መደረጉም ታውቋል፡፡