ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በኢትዮጵያ ባለፉት 24 ሰዐታት ለ2 ሺኅ 844 ሰዎች የላቦራቶሪ ምርመራ ተደርጎ 73 ሰዎች የኮሮና ቫይረስ እንደተገኘባቸው የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ገለፁ።
ቁጥሩ እያሻቀበ በመጣው የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ኢትዮጵያ ውስጥ የሚመዘገቡ ቁጥሮች በከፍተኛ ሁኔታ ቢጨምሩም አሁንም በተለይ በዋና ከተማዋ አዲስ አበባ ግልፅ የሆነ መዘናጋትና ቸልተኝነት እየታየ ነው።
ዛሬ ቫይረሱ ከተገኘባቸው ውስጥ 56ቱ በአዲስ አበባ ሲሆን፤ 4 ሰዎች ከትግራይ ክልል፣ 2 ሰዎች ከአማራ ክልል፣ 8 ሰዎች ከሶማሌ ክልል እንዲሁም 3 ሰዎች የድንበር ተሻጋሪ መኪና አሽከርካሪዎች መሆናቸው በመግለጫው ተጠቁሟል።
በዝርዝሩ ውስጥ ከተካተቱት 27ቱ የውጭ ሃገር የጉዞ ታሪካ ያላቸው ሲሆን ፣ 15ቱ ደግሞ በቫይረሱ ከተያዘ ሰው ጋር ግንኙነት ያላቸው እንዲሁም 31 ሰዎች የውጭ ሃገር የጉዞ ታሪክም ሆነ በቫይረሱ ከተያዘ ሰው ጋር ንክኪ የሌላቸው መሆናቸው ተሰምቷል።
በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ከ6 እስከ 75 አመት ባለው የእድሜ ክልል የሚገኙ 49 ወንድ እና 24ቱ ደግሞ ሴቶች መሆናቸውን የገለፁት የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ፤ ከቫይረሱ 7 አዲስ ሰዎች ማገገማቸውንና አንድ ሰው ደግሞ በፅኑ ህክምና ክትትል ላይ መሆኑን አብራርተዋል።