ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የኮሮና ቫይረስ በፍጥነት ስር እየሰደደባት በሚገኘው ኢትዮጵያ ውስጥ ባለፉት 24 ሰዐታት በኢትዮጵያ 46 ሰዎች ኮቪድ-19 እንደተገኘባቸው ተሰማ።
የጤና ሚንስቴር እና የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በጋራ በሚያወጡት ዕለታዊ መግለጫ፤ ባለፉት 24 ሰዐታት ውስጥ ለ3.410 (ሦስት ሺኅ አራት መቶ ዐሥር) ሰዎች የላብራትሪ ምርመራ ተደርጎ ፤ 29 ወንዶችና 17 ሴቶች በቫይረሱ መያዛቸው ተገልጿል።
ዛሬ በቫይረሱ መያዛቸው ከተመዘገበው ሰዎች መካከል 8ቱ የሚታወቅ የጉዞ ታሪክም ሆነ ከበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር ንክኪ የሌላቸው መሆኑ ተነግሯል። በዚህ መሠረት በአገሪቱ በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋጋጡ ሰዎችን ቁጥር ወደ 701 ከፍ አድርጎታል።
በተያያዘ ዜና ኮሮና ቫይረስ የተገኘባት እና በተጓዳኝ ህመም የህክምና ድጋፍ ሲደረግላት የነበረች የ32 ዓመት ሴት ትናንት ለሊት ሕይወቷ ማለፉን ተከትሎ፤ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ ሕይወታቸው ያለፉ ሰዎች ቁጥርን ስድስት አድርሶታል ሲሉ ዶክተር ሊያ ታደሰ ገልጸዋል።