ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የኮሮና ቫይረስ መስፋፋትን ተከትሎ በአዲስ አበባ ከ10 000 ( ከዐሥር ሺኅ) በላይ የሚሆኑ ሴተኛ አዳሪዎች ተለይተው ድጋፍ መሰጠት ተጀምሯል ተባለ፡፡
የአዲስ አበባ ሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ቢሮ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የተነሳ ለችግር የተጋለጡ ከ10 000 በላይ ሴተኛ አዳሪዎችን እርዳታ ለመስጠት የመለየት ሥራ አካሂጃለሁ ብሏል።
ቀደም ባለው ጊዜ (የኮሮና ቫይረስ ከመግባቱ በፊት) በሆቴሎች፣ በመንገድ ላይ እና በተለያዩ መጠጥ ቤቶች ውስጥ ይሠሩ የነበሩት እነዚህ ሴቶች በኮሮና ቫይረስ የተነሳ ለችግር መጋለጣቸው እየተነገረ ነው፡፡
በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ለችግር ለተጋለጡ ዜጎች የሚደረገው ድጋፍ እነዚህን የኅብረተሰብ ክፍሎችንም ያካተተ እንዲሆን እየተደረገ መሆኑን የከተማዋ ሴቶች፣ ሕጻናትና ወጣቶች ቢሮ ገልጿል።
በአዲስ አበባ ሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ቢሮ የተለዩት ከ10 000 በላይ የሚሆኑ ሴተኛ አዳሪዎች ዝርዝር ሁኔታ ለአዲስ አበባ ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ መተላለፉን እና እርዳታውም በጥቂት ቀናት ውስጥ እንደሚዳረስ ተሰምቷል።
በተመሳሳይ ችግር የሚጋለጡ ሴቶችን በሀገርአቀፍ ደረጃ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ የመጠቁሙ አስተያየት ሰጪዎች ሴቶች እህቶች አብዛኛዎቹ ወደዚህ ስራ የሚገቡት በጭንቀት እንጂ በቅንጦት አለመሆኑን በመረዳት ከጎናቸው መቆም ካልተቻለ ለበሽታው መዛመት ተጋላጭ እንደሚሆኑ አስምረውበታል።
የኢትዮጵያ ሴቶች ሕፃናትና ወጣቶች ሚኒስትር መስሪያ ቤት ጉዳዩን አስመልክቶ በሀገር አቀፍ ደረጃ የመክርበታል ተብሎ ይጠበቃል።