ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– አስቸኳይ አዋጁን የተላለፉ 1.887 (አንድ ሺኅ ስምንት መቶ ሰማኒያ ሰባት) ሰዎችን በአንድ ቀን ምሽት ላይ ባደረገው አሰሳ መያዙን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።
እነዚህ ግለሰቦች ይዞ ምርመራ መጀመሩን እና ቁጥጥሩን አጠናክሮ እንደቀጠለ የገለፀው ፖሊስ ኮሚሽኑ እስከ ግንቦት 17 ቀን 2012 ዓ/ም ባለው ጊዜ ውስጥ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከለካከል የወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በመተላለፍ፣ 4ሰው እና ከ4 በላይ በመሆን በግሮሰሪ፣ ሲጨፍሩና መጠጥ ሲጠጡ፣ ቁማር ሲጫወቱ፣ በቡና ጠጡ ቤቶች ቡና ሲጠጡ እንዲሁም በአንድ ስፍራ ተሰባስበው ጫት ሲቅሙ እና ሺሻ ሲያጨሱ በተገኙ 1.523 ሰዎች ላይ ምርመራውን እንዳጣራም አረጋግጧል።
ምርመራ ተጣርቶባቸዋል ከተባለው ውስጥም 641 ሰዎች በፍርድ ቤት ክስ ተመስርቶባቸዋል። 74ቱ ከ15 ቀን እስከ 3ወር በሚደርስ እስራት፤ 556ቱ ደግሞ እስከ 20ሺ ብር በሚደርስ የገንዘብ ቅጣት እንደተቀጡም ተነግሯል፡፡
በልዩ ልዩ የደንብ መተላለፍ ክስ ከተመሰረተባቸው ግለሰቦች መካከል 11 ግለሰቦች በፍርድ ቤት በገደብ የተለቀቁ ሲሆን፣ 75ሰዎች ላይ አዲስ ምርመራ በማጣራት የምርመራ መዝገቡን ለአቃቤ ህግ ልኮ ውጤቱን በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ገልጿል።
በሌላ በኩል ኮሚሽኑ አሽከርካሪዎች ላይ ባደረገው ቁጥጥር በግማሽ እንዲጭኑ የወጣውን መመሪያ በጣሱ፣ ከታሪፍ በላይ ሲያስከፍሉ በተገኙ፣ ኮድ 2 ሆነው ከተፈቀደላቸው ቀን ውጪ ሲንቃሳቀሱ እና በባለ 2 እግር ሞተር ብስክሌት ላይ ሰው አሳፍረው በተገኙ 5.360 (አምስት ሺኅ ሦስት መቶ ስልሳ) አሽከርካሪዎችን ይዞ በገንዘብ እንዲቀጡ ማድረጉንም ይፋ አድርጓል።