ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የዓለም ጤና ድርጅት በዓለም ዐቀፍ ደረጃ የኮቪድ-19 መድኃኒት ለማግኘት ሲጠቀምበት የነበረውን የፀረ ወባ መድኃኒት፣ “ሃይድሮክሲክሎሮክ”ን ለጊዜው ማቆሙን አስታወቀ፡፡
ተቋሙ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው ከአምስት ቀን በፊት በታተመው “ላንሰት” የተሰኘው የሕክምና መጽሔት ላይ የወጣውን የጥናት ሪፖርት መሰረት አድርጎ መሆኑን ገልጿል።
መድኃኒቱ በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎችን ሞት እንደሚያፋጥኑ በጥናቱ መረጋገጡን ተከትሎ ውሳኔው በፍጥነት ሊተላለፍ ችሏል።
“የከፍተኛ አመራሮቹ ቡድን አባላት የሃይድሮክሲክሎሮክዊን ሙከራ አስተማማኝነት ዳግም በደህንነት ቁጥጥር ቦርዱ እስኪመረመር ድረስ ለጊዜው እንዲቋረጥ ወስነዋል” ሲሉ የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴዎድሮስ አድኃኖም የወባ መከላከያው መድኃኒት ለጊዜው እንዳይመረት መታገዱን አረጋግጠዋል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕና ሌሎች መሪዎች “ሃይድሮክሲክሎሮክዊን” ለኮሮናቫይረስ ሕሙማን ቢሰጥ በፍጥነት እንዲያገግሙ ያደርጋል በሚል በከፍተኛ ደረጃ ሲወደስ እንደነበር ይታወሳል።